ዛሬ ሃያ ሁለት ሰዎች በሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው
ኢትዮጵያ ዛሬ (ሰኞ ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 14, 2016)፦ አቃቤ ሕግ፤ ከኦነግ አመራሮች ተልዕኮ በመቀበል በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኹከት ፈጥረዋል ባላቸው ፳፪ (22) ሰዎች ላይ በሽብርተኝነት ዛሬ ክስ መመስረቱን ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ አስረዳ። ክሱ የተመሰረተው አዲስ አበባ በሚገኘው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፬ኛ ወንጀል ችሎት መሆኑ ታውቋል።
የክስ መዝገቡ የተሰየመው በመጀመሪያው ተከሳሽ በአቶ ደረጀ አለሙ ደስታ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ በአገር ውስጥ በሽብርተኝነት ከተወነጀለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ በተለይም በኖርዌይ እና በኬንያ ከሚገኙ አመራሮች ተልዕኮ ተቀብለው ኹከት አስነስተዋል የሚል ክስ ነው አቃቤ ሕግ የመሰረተባቸው።
አቃቤ ሕግ በአንደኛው ተከሳሽ አቶ ደረጀ አለሙ ደስታ የመሰረተው ክስ፤ ”በ፳፻፮ (2006) ዓ.ም. ኬንያ በመሄድ ኦነግን በመቀላቅል ሥልጥና ወስዶ በ፳፻፰ (2008) ዓ.ም. ሃያ አንድ ሺህ ብር እና አንድ የስልክ ሲም ካርድ በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።
የአቃቤ ሕጉ ክስ፤ ”አዲስ አበባ፣ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና ወረዳ አራት ሐሰተኛ መታወቂያ በማውጣት ወደ ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ከተማ በመሄድ ከአስራ ሦስት እስከ ሃያኛ ያሉ ተከሳሾች ጋር ተገናኘቶ፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ከተማ በአምስተኛ እና ስምንተኛ ተከሳሾች ቤት በተለያዩ ጊዜያት በማረፍ በተለያዩ ቡድኖች በመደራጀት የሽብር መፈጸሚያ አካባቢዎችን ሲያጠኑ ነበር” ይላል ክሱ። ከዚህም ሌላ ታህሳስ አምስት ቀን ፳፻፰ (2008) ዓ.ም. በብቅልቱ አንኮራ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችን በማስተባበር ረብሻ አስነስተዋል የሚል ክስ መካተቱን ለመረዳት ችለናል።
አቃቤ ሕጉ በክሱ ላይ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ውስጥ በኖርዌይ የሚኖሩ ያላቸውን ዶ/ር ደገፋ አብዲሳን የጠቀሰ ሲሆን፤ ዶክተሩ የኦነግ ከፍተኛ አመራር እንደሆኑና በእሳቸው አማካኝነት ሦስት የሽብር ቡድን ታጣቂዎችን ተከሳሾቹ እንዲቀበሉና እንዲያስተናግዱ በታዘዙት መሰረት ተቀብለው ከቡድናቸው ጋር እንዲቀላቀሉ አድርገዋል በማለት የአቃቤ ሕግ ክስ ተከሳሾቹን ይወነጅላል።
ተከሳሾቹ የመንግሥትና የህዝብ ንብረት በማውደም፣ ለመፈጸም ማቀድ፣ ማዘጋጀትና ማሴር እንዲሁም በማነሳሳት የሽብር ወንጀል ነው አቃቤ ሕግ ክሰ የመሰረተባቸው። ተከሳቾቹ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ለኅዳር ፲፮ (16) ቀን ፳፻፱ (2009) ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።