ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ነጻነት በዓለም ከመጨረሻዎቹ አራተኛ ሆነች

ኢትዮጵያ ዛሬ (ኀሙስ ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 17, 2016)፦ ኢትዮጵያ ኢንተርኔት በማግኘት ነጻነት ከዓለም አገራት ከመጨረሻዎቹ በአራተኝነት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ”ፍሪደም ኃውስ” የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣው ዓመታዊ ሰነድ መጠቆሙን ኳርትዝ አፍሪካ ዘገበ። ከአፍሪካ የመጨረሻዋ አገር እንደሆነች ታውቋል።
በዓለም ላይ ካሉ አገራት ኢንተርኔት በማግኘት ነጻነት፣ በሳንሱር እና መረጃ በማግኘት ነጻነት ዙሪያ በተደረገው መለኪያ ኢትዮጵያ የምትበልጣቸው ብቸኞቹ ሦስቱ አገራት ኢራን፣ ሶርያ እና ቻይና መሆናቸው ታውቋል። ኢትዮጵያ ኢንተርኔት በማግኘት ነጻነት ከአፍሪካ የመጨረሻዋ አገር ስትሆን፤ መንግሥት አልባዋ ሶማሊያን እንኳን መብለጥ የተሳናት አገር መሆንዋ ዜግዎችዋን ያሳፈረ ጉዳይ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ያነጋገራቸው በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገልጠዋል።
አስራ ሁለት ከመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ነዋሪ የሞባይል ተጠቃሚ ሲሆን፣ ሞኖፖሊስቱ ኢትዮቴሌኮም ኢንተርኔት ለማግኘት ከጎረቤት አገሮች ከዩጋንዳና ከኬንያ በሦስት እጥፍ ክፍያ እንደሚያስከፍል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የቴሌፎንና የኢንተርኔቱን አገልግሎት በብቸኝነት (በሞኖፖል) የተቆጣጠረው የኢትዮቴሌኮም ድርጅት፤ የቻይናውያኑ ዜድቲኢ እና ኋዋዪ ድርጅቶች የሞባይል እና የብሮድባንድ (ኢንተርኔት) ስርጭትን ለማስፋፋት ኮንትራት የተሰጣቸው ቢሆንም፤ ከተፈራረሙት የሥራ ኮንትራክት ይልቅ በሥልጣን ላይ ላሉት ወገኖች የሳንሱር ተግባር እና ሲቪል ሰዎችን ለመሰለል እያገዟቸው ከመሆኑም ባሻገር የዜጎችን በነጻነት ኢንተርኔ የመጠቀምና መረጃ የማግኘት መብትን እየነፈጉ መሆኑን ጉዳዩን በአንክሮ የሚከታተሉ ወገኖች ይተቻሉ።



