PM Dr Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ “መደመር” መጽሐፍ ምርቃት ላይ ንግግር ሲያደርጉ (ዓርብ ጥቅምት ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 19, 2019)

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስም ሳይጠቅሱ ለሕወሓት ምላሽ ሰጡ፤ “50 ሚሊየን ሕዝብ መጠለያ በሌለው አገር ውስጥ በ10 ሰው ስም ፎቅ ደርድረህ አስብለሃለሁ ብትለው ሥላቅ ነው”

ኢዛ (ቅዳሜ ጥቅምት ፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 19, 2019):- ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከኢሕአዴግ ውሕደት ጋር በተያያዘ መዋሐድ ኢትዮጵያን የሚጨፈልቅ፣ እልቂት ያስከትላል በሚል በአንዳንድ ወገኖች እየተነገር ያለውን አመለካክት የተሳሳተ ስለመኾኑ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይኽንን የገለፁት ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ “መደመር” የሚለውን አዲሱና አምስተኛው መጽሐፋቸው በተመረቀበት ወቅት ነው።

ዛሬ የተደረገውን የምረቃ ፕሮግራም እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ባደረጉት ንግግር፤ ስለኢሕአዴግ ውሕደት ጉዳይ ቀድመው እየተገፁ ያሉ እርሳቸው “መርዶ” ያሉትን አፍራሽ መግለጫዎች ያልተገቡ ስለመኾናቸው ጠንከር ባሉ ቃላቶች መልስ የሠጡበት ነበር።

ይህንንም ሲገልጹ፤ “ከፓርቲ ውሕደት ጋር ተያይዞ ብዙ ሐሳቦች ሲነሱ ስለምሰማ፤ ይሔ መጀመሪያ ያገኘኹት እድል ስለኾነ እዚህም ያለው ስብስብ ቀላል ስላልኾነ ለመላው ኢትዮጵያውያን ይህንን ጉዳይ በአጭሩ መግለጽ እፈልጋልኹ” በማለት ነበር ገለጻቸውን የጀመሩት።

የፓርቲው የውሕደት ጉዳይ አላለቀም፤ እኛ የመደመር ፍልስፍናን የምናምን ሰዎች በዴሞክራሲያዊ ውይይት ስለምናም፤ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ሰነድ ቢኾንም ላለመበተን ስንለማመንና ስንወያይ ከርመናል ብለዋል።

አሁንም ውይይቱ ያለመቋጨቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ውይይቱ ሳይቋጭ አንዳንዶች ይህ ውሕደት መጨፍለቅ ነውና ኢትዮጵያን ከፌዴራል ሥርዓት ወደ አኀዳዊ ሥርዓት መመለስ ነው የሚል በኛ ውስጥ ታስቦና ታልሞ የማያውቀውን መርዶ አረዱን ብለዋል።

የፓርቲው አንድ መኾን ኢትዮጵያን የሚጨፈልቅ ከኾን፤ ኢትዮጵያ አልነበረችም ተጨፍልቃለች ማለት መኾኑን በመጠቆም፤ ለዚህ አባባላቸው እንደ መረጃ የጠቀሱት፤ በተለያዩ ክልልሎች ያለውን አስተዳደር ሁኔታ ነበር። ከነዚህ ውስጥ አንዱን በዚህ መልክ ገልጸውታል፤ “ትግራይ ውስጥ ቲፒኤልኤፍ (TPLF/ሕወሓት) የሚባል ድርጅት እንጂ ኩናማ የራሱ ድርጅት የለውም፤ ኢሮብ የራሱ ድርጅት የለውም። ኢሮብ የራሱ ልዩ ወረዳ አለው። ኩናም የራሱ ወረዳ አለው። በቲፒኤልኤፍ ይተዳደራል። ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓት አልተጨፈለቀም።”

“አንድ ፓርቲ 50 ብሔር ብሔረሰቦች ማስተዳደር ከቻለ፤ እንዴት ነው አንድ ፓርቲ መጨፍለቅ የሚችለው፤ እንዴትስ ነው እኛ ኢሕአዴጎች ለ30 ዓመታት አንድ መኾን ተስኖን ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ የምንችለው?!

“የትናንትናውን ስሕተት እናርማለን ስንል፤ ኢሕአዴግ ላለፉት ዓመታት ሕገመንግሥቱን በብዙ መንገድ ሲጥሰው ቆይቷል። ከዚያ ውስጥ አንዱ ሕገመንግሥቱ “አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር” ቢልም፤ እንኳን ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ፤ እራሱም አንድ መኾን ተስኖት ቆይቷል” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሌላም አሳዛኝ ነገር አለ ይላሉ።

አሳዛኝ ያሉትን ሁኔታ ደግሞ፤ “ሌላው የሚያሳዝነው መደመር ፍልስፍና ከኾነና ፓርቲው የሚዋሐድ ከኾነ ወደ እልቂት እንገባለን የሚለው ጉዳይ ነው። እልቂትን ምን አመጣው?!” በማለት፤ “አንድ ፓርቲ መኾንና “መደመር” የማያዋጣ ከኾነ፤ ጀግና ሰው ውስኪውን አስቀምጦ “መባዛት” የሚል አማራጭ ሐሳብ ይዞ ይመጣል።” በሚል አንድ መኾን እልቂት ይፈጥራል የሚለውን አመለካከት ተገቢ ያለመኾኑን አመላክተዋል።

በመኾኑም፤ መደመርና መባዛት የሚለው ሐሳብ ቀርቦ ሕዝብ ይወስንበታል እንጂ፤ መገዳደል አስፈላጊ ያለመኾኑንም በዚሁ ንግግራቸው አጽንኦት ሠጥተው ተናግረዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በሰነዘሩት ሐሳብ እኔ ያልኩት ካልኾነ የሚቀጥለው አማራጭ መገዳደል ነው የሚለው የ19ኛው ክፍለ ዘመን፤ የነማርክስና የሌሊን እሳቤ እንጂ የመደመር ሐሳብ ያለመኾኑንም አመልክተዋል።

መደመር የሚያም ነው ብለው የሰነዘሩት ደግሞ፤ “እኛ ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች፤ እባካችሁን ውኃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ ይላል መደመር” በማለትም ገልጸዋል።

መደመር ሌብነትን ቀይ መስመር ያለበት ምክንያት፤ በስም፣ በአጎት፣ በአክስት፣ በምናምን … አዲስ አበባ ላይ ፎቅ መደርደር ብቻ ሳይኾን፤ ዱባይ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ ደርድረህ፤ ቤት አልባውን ሕዝብ፣ 50 ሚሊየን ሕዝብ መጠለያ በሌለው አገር ውስጥ፤ አንተ በአሥር ሰው ስም ፎቅ ደርድረህ፤ “አስብለሃለሁ” ብትለው ሥላቅ ነው።

“ከዓመት ዓመት ሆቴል ተቀምጥህ፣ ሆቴል እየተመገብክ፤ በአምስት ሺሕ ብር ደምወዝ፤ ምንጩን እግዚአብሔር ይወቀው! ዳቦ የራበውን ሕዝብ፤ “ላንተ ቆሜልሐለሁ” ማለት ተረት ተረት ነው” በማለት በሌብነት የተዘፈቁትን ኢሕአዴጋውያን፤ በተለይም ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ለቀለዱት ጠንካራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብም፤ “በሰሜን፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ፣ ደቡብ ያላችሁ የተማራችሁ፣ የተሻለ ማገናዘብ የምትችሉ ወጣቶች፤ የምንቀልድባችሁን ቀላጅ ፖለቲከኞች ወደጎን አራግፋችሁ፤ አገራችሁን ጠብቁ!” በማለት አደራ ሠጥተዋል።

“የተሠጠውን እድል መጠቀም ሳይችል፤ እድል ሲነጠቅ በጀነሬሽን እድል መቀለድ አይቻልም!” በማለት ዶ/ር ዐቢይ ያላቸውን ግልጽ አቋም አስረግጠው ተናግረዋል።

የኢሕአዴግ ውሕድ መኾን ጠቀሜታንም በሠፊው ያብራሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በትውልድ ላይ መቀለድ ይብቃም በማለት በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ዜጎች መደመር ብልጽግናን ይወዳል በማለት፤ ብልጽግናን እንደሚያውጁም ተናግረዋል።

“ብዙዎች የብልጽግና ጉዞ የሚደናቀፍ፣ የሚቆም ይመስላቸዋል” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ “ዛሬም በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ የምወደው ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ካለችበት ሁኔታ ከፍ ትላለች፤ ኢትዮጵያ እንዳትበለጽግ የሚፈልጉ ይጠፋሉ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና አይጠፋም” የሚል መልእክታቸውን ያስተላለፉበት መድረክ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የፓርቲው ውሕደት በመቃወም መርዶ ያረዱናል ያሉትን በስም አልጠቀሱም። ኾኖም በውሕደቱ ላይ በይፋ አልቀበለውም በማለት በመግለጫ ያሳወቀው ሕውሓት መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!