የተንቤን ነዋሪዎች ጠ/ሚ/ር መለስን ወቀሱ
Ethiopia Zare (ዓርብ መስከረም ፪ (2) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 12, 2008)፦ጠ/ሚ/ር መለስ ተንቤንን ሲጎበኝ የከተማው ነዋሪ ”… ግንባር ቀደም ሆነን ታግለናል፣ ልጆቻችንን መሥዋዕት አድርገናል፣ ታዲያ ለምንድነው ያገለልከን? የመጣኸበትን መንገድ አይተኸዋል? ለሌሎች ክልሎች በጀት መድበህ እንደምታስገነባው ሁሉ ለምን ለእኛም እንደዛ አታደርግም? ስንዴ መጥቷል ተባልን ነገር ግን እንደሌሎቹ በገንዘባችን እንኳን ማግኘት አልቻልንም፣ በረሃብ እያለቅን ነው፣ ይኼ ሁሉ ሲሆን ዝም ብለህ የምታየን ለምንድነው? …” ሲል ተቃውሞውንና ቅሬታውን በማሰማት ጠ/ሚ/ር መለስን ወቀሰ።
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኢህአዴግን ጉባዔ ባለፈው ዓመት ነኀሴ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ክልል ያመራው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ተምቤን ከተማ ባደረገው ጉብኝት ከነዋሪው ወቀሳ ገጥሞታል።
ጠ/ሚ/ሩ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተዘዋውሮ ያነጋገረ ሲሆን፣ ተምቤን በሄደበት ወቅትም አዲስ የተሠሩ ኮንድሚኒየም ቤቶችን ከጎበኘ በኋላ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ለመረዳት ችለናል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የከተማው ነዋሪዎችም ”… ግንባር ቀደም ሆነን ታግለናል፣ ልጆቻችንን መሥዋዕት አድርገናል፣ ታዲያ ለምንድነው ያገለልከን? የመጣኸበትን መንገድ አይተኸዋል? ለሌሎች ክልሎች በጀት መድበህ እንደምታስገነባው ሁሉ ለምን ለእኛም እንደዛ አታደርግም? ስንዴ መጥቷል ተባልን ነገር ግን እንደሌሎቹ በገንዘባችን እንኳን ማግኘት አልቻልንም፣ በረሃብ እያለቅን ነው፣ ይኼ ሁሉ ሲሆን ዝም ብለህ የምታየን ለምንድነው? …” ሲሉ የወቀሱት መሆኑ ተደምጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከመንገድ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክቶ፤ ከመቀሌ - ዓብይአዲ - ዐድዋ ያለውን መንገድ አስፋልት እንደሚለብስና ሌሎች ጉዳዮችም እንደሚያስተካክል ለተንቤን ከተማ ነዋሪ ቃል ገብቷል።
ጠ/ሚ መለስ ከጉባዔው በኋላ በሰጡው መግለጫ በከተማና በገጠር መሠረታዊ የአስተዳደር ብልሽትና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ የመሬት አስተዳደር ችግር መሆኑን ገልጾ፣ ይህ ሥርዓት መልክ ይዞ እንዲሄድ በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ቁልፍ ጥያቄ መሆኑን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገጠርና በከተማ ያሉት የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ትክክለኛ አቅጣጫ ይዘው የሚፈለገው ደረጃ መድረስ እንዳለባቸው አመልክቷል። መልካም አስተዳደር ሲባል በህዝቡ ቅሬታ የማያሳድር እና ስሕተት የማይፈጽም አስተዳደር ይፈጠራል ማለት ሳይሆን፤ በአብዛኛው ፍትሃዊ ውሳኔ የሚሰጥ አስተዳደር ለማቋቋም ጥረት ይደረጋል ማለት እንደሆነ አብራርቷል።