ከሕወሓት የተፋቱት አቶ ዛዲግ በሚኒስትር ማዕረግ ተሾሙ
አቶ ዛዲግ አብርሃ
ሿሚው ጠ/ሚ ዐቢይ ናቸው
ኢዛ (ረቡዕ ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 29, 2020)፦ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አባል በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩትና ይፋዊ በኾነ መንገድ ከሕወሓት መልቀቃችውን ያሳወቁት አቶ ዛዲግ አብርሃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተሾሙ።
ዛሬ ይፋ በኾነው መረጃ ሕወሓትን በመቃወም ከፓርቲው ራሳቸውን አግልለው የቆዩት አቶ ዛዲግ አብርሃ ዛሬ የተሠጣቸው ሹመት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ ኾነው እንዲያገለግሉ ነው።
አቶ ዛዲግ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ከሚጠቀስላቸውና በኃላፊነት ከቆዩባቸው ሥልጣናቸው ውስጥ አንዱ፤ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዲኤታ እንደኾነ አይዘነጋም። (ኢዛ)



