Ethiopian Parliament

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የጥላቻ ንግግርን ለሚመለከተው አዋጅ፤ 23 የፓርላማ አባላት የተቃውሞ ድምፅ ሠጥተዋል

ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 13, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የኤክሳይዝ ታክስ”ና “የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል” በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁትንና እጅግ አከራካሪ የነበሩትን አዋጆች ዛሬ በአብላጫ ድምፅ አጸደቀ።

ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች የጸደቁት እነዚህ ሁለት አዋጆች፤ ማሻሻያ የተደረገባቸው ናቸው የተባሉ አንቀፆች ተካትተውባቸው የጸደቁ ሲሆን፤ ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀፆችና የአዋጆቹ አስፈላጊነት ተብራርቷል።

እነዚህ ሁለት አዋጆች ከሌሎች ረቂቅ አዋጆች በተለየ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በባለድርሻ አካላት ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩባቸው ናቸው። በተለይ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን የተመለከተው አዋጅ፤ ኪሣራ የኾኑ አንቀፆችን ያካተተ ስለመኾኑ ተጠቅሶ ተቃውሞ ሲቀርብበት የቆየ ነው።

ረቂቅ አዋጁ አሁን ባለው መልኩ መጽደቅ የለበትም ወይም ጭርሱኑ ይህ አዋጅ አያስፈልግም እስከማለት ሙግት የቀረበበት እንደነበር አይዘነጋም። ይህ መንፈስ ዛሬም በምክር ቤቱ ውስጥ ተንጸባርቋል።

ኾኖም ዛሬ ፓርላማው በረቂቅ አዋጁ ላይ በመወያየት አዋጁ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል። ነገር ግን ይህ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ይጽደቅ እንጂ፤ የአዋጁን መጽደቅ የተቃወሙ 23 የምክር ቤት አባላት ነበሩ። ሁለት አባላት ደግሞ ድምፀ ተዓቅቦ አድርገዋል።

በምክር ቤቱ ውስጥ በዚህን ያህል ተቃውሞ ቀርቦበት የጸደቀ አዋጅ እንደሌለም ይነገራል። የኤክሳይዝ አዋጁ ደግሞ በአራት ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ