የመጠጥ ፋብሪካዎች ከ48 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ አደረጉ
የቢራና የድራፍት ዋጋ ከ48 በመቶ በላይ ጨመረ
የቢራ ፋብሪካዎች በአንድ ሣጥን ቢራ 140 ብር ጨምረዋል
ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 18, 2020)፦ ሰሞኑን ከጸደቀው ኤክሳይዝ ታክስ ጭማሪ የመጠጥ ፋብሪካዎች ዋጋ መጨመራቸው እየተገለጸ ነው። የቢራ ፋብሪካዎች በአንድ ሣጥን ቢራ 140 ብር ጨምረዋል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ከተለያዩ ሆቴሎችና ቡና ቤቶች ባለቤቶች መረዳት እንደቻለው የቢራና የድራፍት የፋብሪካዎች የሚያከፋፍሉበት ዋጋ ላይ ወደ 50 በመቶ ጭማሪ አድርገዋል። በዚህም መሠረት በቀድሞው የማከፋፈያ ዋጋ ላይ በአንድ ሣጥን የቢራ ምርቶች ላይ 140 ብር፣ በአንድ በርሜል ላይ ደግሞ ከ345 ብር በላይ ጨምሯል።
ቀድሞ አንድ ሣጥን ቢራ (24 ፍሬ ቢራዎች) 290 ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን 430 ብር ኾኖአል። በዚህ ስሌት መሠረት ከ48 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ታውቋል። አንድ በርሜል ድራፍት 815 ብር የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ጭማሪ 1 ሺህ 160 ብር በመኾኑ ከ42 በመቶ በላይ ፋብሪካዎቹ ጭማሪ ማድረጋቸው ታውቋል።
በትናንትናው ዕለት አብዛኞቹ ሆቴሎች በሁሉም ቢራዎች ላይ ጭማሪ አድርገው ሲሸጡ የነበሩ መኾኑን ለመረዳት ችለናል። በዚሁ መሠረት አንድ ጠርሙስ ቢራ በሆቴሎችና ቡና ቤቶች የችርቻሮ ዋጋው በአማካይ 15 ብር የነበረ ሲሆን፣ ከትናንት ጀምሮ ዋጋው ከ20 እስከ 30 ብር መድረሱ ታውቋል።
አብዛኞቹ የመጠጥ ፋብሪካዎች፤ በተለይም የቢራና ድራፍት ፋብሪካዎች የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ሄይኒከን ቢራ ጭማሪ አለማድረጉን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የፋብሪካውን ኃላፊዎች አናግሮ ለመረዳት ችሏል።
አከራካሪ የነበረው የኤክሳይዝ ታክሱ አዋጅ የጸደቀው ባለፈው ሐሙስ የካቲት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ መኾኑን መዘገባችን አይዘነጋም። አዋጁ የጸደቀው በአብላጫ ድምፅ ሲሆን፣ 4 ተቃውሞና 7 ድምፀ ተዓቅቦ ገጥሞት ነበር። አዋጁ ከየካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባር ላይ መዋሉ ይታወቃል።
ተጨማሪ ዜና፤
ይህ ዜና ተጠናክሮ ለንባብ ከወጣ በኋላ ዛሬ አመሻሹ ላይ ባደረግነው የዋጋ ማጣራት እንደሚከተለው ይገኛል።
ዋልያ ድራፍት የአንድ በርሜል ዋጋ ከ815 ብር ወደ 1160 ብር፣
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድራፍት የአንድ በርሜል ዋጋ ከ815 ብር ወደ 1165 ብር፣
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ የሣጥን (24 ፍሬ) ዋጋ ከ290 ብር ወደ 430 ብር፣
ዋልያ ቢራ የሣጥን ዋጋ ከ290 ብር ወደ 430 ብር፣
ሐበሻ ቢራ የሣጥን ዋጋ ከ290 ብር ወድ 415 ብር ከፍ ማለታቸው ታውቋል።
የሄይኒከን ቢራም የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ለማረጋገጥ ችለናል። ፋብሪካው ከሚያመርታቸው ምርቶች ውስጥ ራሱ ሄይኒከን፣ ዋልያና ሐረርና በደሌ ይገኙበታል። ቢጂአይ ኢትዮጵያ የተባለው ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ዛቢዳር፣ ራያና ካቴልን የሚያመርት መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)



