ከጥር 4 - 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ ዘጠነኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥር 4 - 10 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ዐቢይ ዜና በመኾን በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ነው። ቦርዱ ያሰናዳውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከረበትም ወዲያው ነው። ይሁንና የጊዜ ሰሌዳው በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሠጠበት ይገኛል። እነዚህ አስተያየቶች በርካታ ጉዳዮችን እያመላከቱ ነው። ቀጣዩን የምርጫ ሒደት በምን መልኩ ይካሔድ የሚለውን አመለካከት የተለያየ እንዲሆን አድርጓል። ምርጫ ቦርድ ግን የተጣበበውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ በማመን፤ የጊዜ ሰሌዳውን በማውጣት እንዲመከርበት ማድረጉ በትክክል ምርጫው ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ የሚካሔድ መኾኑን ያሳየበት ስለመኾኑም ተገልጿል።

በአንፃሩ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ምርጫው ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. መኾኑ ግን በብዙዎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል። ቅሬታ ብቻ ሳይሆን በተጠቀሰው ቀን ምርጫ ለማድረግ ፈጽሞ የማይመች መኾኑን በመግለጽ ተቃውመውታል።

ያሳለፍነው ሳምንት ከሌሎች ሳምንታት በተለየ በርከት ያሉ አንኳር ወሬዎች የተስተናገዱበት ነበር። ከዚህ ውስጥ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተለይም በውኃ አሞላል ላይ ዋሽንግተን በሦስቱ አገሮች የተካሔደው ውይይትና የውይይቱ ውጤት ምን ያስገኝ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ በመያዝ ብዙ ሲባልበት ሰንብቷል።

ሌላው ብዙ ዓይንና ጆሮ አግኝቶ በዐበይት ሳምንታዊ ክስተት ተርታ የሚቀመጠው በትግራይ ክልል መንገድ በመዝጋት ጭምር የተደረገ ተቃውሞ ነው። እንዲህ ባለመንገድ ተቃውሞ በትግራይ መደረጉ እንደ አዲስ ክስተት የታየ ሲሆን፤ የህንጣሎ አካባቢ ነዋሪዎች የወረዳ እንሁን ጥያቄያቸው ይመለስ ዘንድ የተደረገው ተቃውሞ ለቀናት የመዝለቁ ነገር ትኩረት የሳበ ዜና ኾኗል። ከዚሁ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ አስገራሚው ነገር እንዲህ ባለው ደረጃ የተደረገ እንቅስቃሴ ላይ የትግራይ ክልል መንግሥት ምንም አለማለቱ ነው።

አነጋጋሪ በመኾን ሳምንታት የተሻገረውና ባሳለፍነው ሳምንትም አነጋጋሪነቱ የቀጠለው የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “እገታ” ጉዳይ ነው። ታግተዋል በተባሉት ተማሪዎች ዙሪያ እየተሠራጩ ያሉ መረጃዎች አወዛጋቢነት አሁንም ቀጥሏል። በተለይ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ሲሠጡ የነበሩ መረጃዎች ሁኔታውን እያወሳሰቡት ነው።

የጋሞ አባቶች የሰላም ጉዞ ሌላው ዜና ነበር። ከዩኒቨርሲቲ ግጭቶች ጋር ያሉ ችግሮች ዛሬም ሙሉ በሙሉ ያልተፈቱ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ስለመቀጠሉ እየተገለጸ ነው። በየዩኒቨርሲቲዎቹ በተፈጠሩ ችግሮች እጃቸው ያለባቸው ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ ተወሰደ የተባለው እርምጃም በአኀዝ ጭምር እየተገለጸ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የመንግሥት እርምጃ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ከሥራ እስከማገድ የደረሰ መኾኑን በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ከሥራ ስለመታገዳቸው መነገሩ በምሳሌነት ይጠቀሳል።

ለሳምንታት አነጋጋሪ የነበረውና ብዙ ሲባልለት የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ መንግሥት ማሻሻያ ያደረገባቸውን የረቂቅ አዋጁን ክፍል ይፋ ያደረገበት መግለጫ የተሠጠው በዚሁ ሳምንት ነው። ከተለያዩ አቅጣጫዎች የቀረቡትን አስተያየቶች መሠረት በማድረግ መንግሥት እንዲሻሻል ካደረገባቸው የረቂቅ አዋጅ ክፍል በአነስተኛ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ ወደ አምስት በመቶ ማውረዱ አንዱ ነው። ሌሎች ማሻሻያ የተደረገባቸውን የረቂቅ አዋጁ አንቀፆችንም አስታውቋል።

እነዚህና ሌሎች ክስተቶችን ያስተናገደው ካሳለፍነው ሳምንት ዜናዎች የተወሰኑትን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምልከታ በማድረግ እንደሚከተለው በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ቀርቧል።

ቀጣዩ ምርጫና የጊዜ ሰሌዳው እያስነሳ ያለው ጥያቄ

ኢትዮጵያ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ታካሒዳለች አታካሒድም የሚለው ጥያቄ ብዙ ሲባልበት ነበር። አንዳንዶች አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫውን ማድረግ ተገቢ አይሆንም ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ምርጫው መደረጉ የግድ ስለመኾኑ አፅንኦት ሠጥተው ይከራከራሉ። ከምርጫ ቦርድ የተሰማው ዜና ግን ያለውም ጊዜ በመጠቀም አገራዊውን ምርጫ ለማካሔድ ቁርጠኛ ስለመኾኑ የሚያሳይ ሆኗል።

ይህም የቀጣዩን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ነው። ይፋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን እንዲመከርበት ማድረጉ ነው። በጊዜያዊ የምርጫ ቦርድ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጫ ቀኑ ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚኾን ታውቋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ እና አፈፃፀሙ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር አድርጐት በነበረው ውይይት ላይ ከተሳታፊዎቹ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የመራጮች ምዝገባ ጊዜ 30 ቀናት ኾኖ በመቅረቡ አግባብ ያለመኾኑና ይህ የተጠቀሰው ጊዜ ያንሳል መባሉ አንዱ ነው።

የእጩ ምዝገባ ቀናትም በተመሳሳይ በቂ ያለመኾኑን የገለጹም አሉ። በተለይ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱና ትችትም የሰነዘሩበት ጉዳይ ድምፅ የሚሠጥበት ቀን ክረምት ላይ ከመኾኑ ጋር የተያያዘ ነው። ቦርዱ ባስቀመጠው የምርጫ ሰሌዳ ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ክረምት በመኾኑ ምርጫውን ለማስፈጸም የማያስችል እንደኾነ በመግለጽ፤ የተመረጠው ቀን ትክክል እንዳልኾነ አስረድተዋል። ቦርዱም ቢሆን ምርጫውን ለማስፈጸም ይቸገራል። እንዲህ ባለው ጊዜ ምርጫውን ማካሔዱ ተገቢ አለመኾኑን ተናግረዋል። ከሌሎች ጉዳዮች የበለጠ ይህ ለድምፅ መስጫ የተመረጠው ቀን ላይ ነው የብዙዎች ተቃውሞ። አንዳንዶች ይህ ከሚኾን ምርጫውን ወደ ጥቅምትና ኅዳር ወር መግፋት አለበት የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

ወንዝ መሻገር በማይቻልበት በዚያ ወቅት ምርጫ አድርጉ መባሉ ትክክል አለመኾኑን በመግለጽ፤ አሁንም አማራጮች መታየት አለባቸው ያሉም አሉ።

ከዚህ ባሻገር የምረጡኝ ቅስቀሳ ቀናት ያንሳሉ፣ ከአሁን ጀምሮ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎችም አሉ፣ ቦርዱ ምን ለማድረግ አስቧል፣ ፓርቲዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚደራደሩበት ቅደም ተከተል በእጣ ይሆናል ማለት ምን ማለት ነው? በሚሉና ሌሎቹ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤ በቦርዱ አመራር የመራጮች ምዝገባ በሕግ የተቀመጠው 30 ቀን በመኾኑ በዚሁ መሠረት መካሔድ የሚችል መኾኑን ነው። የእጩ ምዝገባ ቀናትን አስፈላጊ ከኾነ ቀናት መጨመሩን ቦርዱ ሊያየው እንደሚችል ያመለክታል። ሆኖም በእቅዱ ላይ የተቀመጠው ቀን ለፓርቲዎች እንደሚያንስና እንዲያውም ጫና የሚኾነው ቦርዱ ላይ በመኾኑ ቀኑ አነሰ የሚለው ብዙ አከራካሪ አይሆንም።

ነኀሴ ላይ ምርጫው መካሔዱ ቦርዱ ወዶ የገባበት አይደለም፤ ግንቦት ወር ላይ ለማድረግ ስላልተቻለ ነው፣ ብዙ የተዘረዘሩ ለውጦች እያደገ እንደኾነ ቦርዱ ገልጿል። ስለዚህ ግንቦት ላይ ማድረግ የሚቻል አይደለም። አፈፃፀሙ ክረምት በመኾኑ ብዙ ችግር እንደሚገጥመው እሙን ነው፤ ከክልል መንግሥታት፣ ከፌደራል መንግሥትና ሌሎች ተቋማት ቦርዱ የሎጀስቲክስ ድጋፍ ጠይቆ ለማስፈፀም ጥረት ያደርጋል። ከመስከረም ካለፈ ደሞ የሕግ ጥሰት ይፈጥራል፤ ስለዚህ ወደፊት መግፋት ስላልተቻለ የኾነ መኾኑን ቦርዱ በሠጠው ማብራሪያ ላይ አመልክቷል።

የምረጡኝ ቅስቀሳ አሁን መጀመር አይችልም፤ የተሰጠው ሦስት ወር በላይ ግን በቂ ነው፣ ከአሁኑ ቅስቀሳ የጀመሩ አሉ ለተባለው ውይይትና ንግግር ከሕዝብ ጋር ማድረግ ይቻላል፣ እኔን ምረጡኝ የሚል ዘመቻ ግን መጀመር አይቻልም፣ ያንን የሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ቦርዱ ማጣራት እንደሚያደርግ አሳውቋል።

በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ከተሠጡ አስተያየቶች ውስጥ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ያለውን የፀጥታ ችግር የገለጹ አሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ምክክር መድረክ ሰብሳቢ ደግሞ የምርጫው ሰሌዳ መውጣት መልካም ነገር ሆኖ፤ ድምፅ የሚሠጥበት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንፃር ክፍተት ሊኖረው እንደሚችል ገልጸዋል።

እንደ እሳቸው አመለካከት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲያቸው ውስጥ ድምፅ እንዳይሠጡ የምርጫ መስጫ ተብሎ የተጠቀሰው ቀን ዩኒቨርሲቲዎች ለዕረፍት ከተዘጉ በኋላ መኾን ያስቸግረዋል። በትውልድ ቀያቸው እንዳይሠጡም ለዕረፍት ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ጉዞ ላይ ስለሚኾኑ የምርጫ ተሳትፏቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ አሁንም ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለንም ብለው ሞግተዋል። ምርጫው ግብ ተደርጐ መወሰድ የለበትም ይላሉ እነዚሁ ወገኖች። ምክንያታቸው ደግሞ ምርጫ ለማድረግ ብቻ ምርጫው መካሔድ የለበትም የሚል ሲሆን፤ አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ አንፃር ምርጫው ይካሔድ እንኳን ቢባል ይዞ የሚመጣው ነገር መልካም አይሆንም የሚል ሥጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

እንደነ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉ ደግሞ ጭርሱኑ ምርጫው አሁን አገሪቷ ካለችበት ሁኔታና ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ማድረጉ ተገቢ አለመኾኑን ይሞግታሉ።

እንደ አገር ምርጫ ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ነን ወይ? የሚለውን ጥያቄ በማስቀደም አስተያየት የሠጡት አቶ ልደቱ፤ ሕጋዊነትን በመጥቀስ ምርጫው በተገለጸው ጊዜ መካሔድ አለበት የሚለው ላይ የተለየ አመለካከት እንዳላቸው፤ በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ የውይይት መድረክ ላይ ገልጸዋል።

“ያለንበት ወቅት ድህረ ፖለቲካዊ ቀውስ መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ልደቱ፤ የምርጫ ቦርድ አባላት ይሄ ታሪካዊ ኃላፊነት እጃችሁ ውስጥ የገባው በአንድ ታሪካዊ ሒደት ነው። ያለንበት ወቅት የለውጥ ሒደት ከኾነ ይህ ሒደት የመጣው ሕግ ተጥሶ ነው የሚልም እምነታቸውን አንጸባርቀዋል።

የኢትዮጵያ ሕግ ማንም አካል በመንግሥት ላይ ማመፅ አይችልም። ወደ ሥልጣን የሚመጣው በሠላማዊ መንገድ ብቻ ነው እንደሚል በማስታወስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታግሎ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ይህ ለውጥ ሕግ መጣስ ስለነበረበት ሕግ ተጥሶ የመጣ ነው የሚሉት አቶ ልደቱ፤ ምርጫው መካሔድ የሌለበት ወደሚል እምነት የገቡባቸውን የተለያዩ ምክንያቶች አብራርተዋል። ይህንንም ሰላምና የሕግ የበላይነት ስለሌለ እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሔድ አይቻልም። ሕዝብ መቁጠር ያልቻለ መንግሥት እንዴት አድርጐ ምርጫ ያደርጋል? በማለት የሚጠይቁት አቶ ልደቱ ሕብረተሰቡ የሰላም ሥነ ልቦና ያስፈልገዋል ብለዋል።

ሕዝቡ የጠየቀውም የለውጥ ሒደት ባለመሳካቱ እንደኾነም የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጭ ብለን መፍታት ያለብን በመኾኑ፤ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ ምርጫ ማድረግ ወደኋላ የሚመልስ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

ሌላው ምርጫውን ለማካሔድ በቂ ዝግጅት ባለመኖሩ የሚታየው ግጭት ማቆሚያው የማይታወቅና መንግሥትም ይህንን ለማስቆም ይህንን አደርጋለሁ ባላለበት ሁኔታ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ የምርጫ አዋጅ ለመመዝገብ ማሟላት ያለባቸው እንደ 10 ሺሕ አባላት አስፈርሞ ማምጣትን የሚጠይቅ በመኾኑ፤ እንዲህ ያሉት ሁኔታዎችና ችግሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲህ በቀላሉ ምርጫውን ለማድረግ መነሳት ተገቢ እንዳልሆነ አመላክተዋል።

የዝግጅቱ ጉዳይ ምርጫ ቦርድንም የሚመለከት በመኾኑ በተለይ በክረምት ወቅት ምርጫ ማካሔድ የማይቻል ስለመኾኑም በማመልከት፤ አሁን ያለው የተጣበበ ጊዜ በሁሉም መልኩ በበቂ ዝግጅት የማይካሔድ በመኾኑ ምርጫው መካሔድ የለበትም ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል።

የአቶ ልደቱንና ሌሎች አስተያየቶችን መሠረት በማድረግ ከምርጫ ቦርድ የተሠጠው ምላሽ፤ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንደሚኖርበት፣ ምርጫ ቦርድም በተሠጠው ኃላፊነት መሠረት እየሠራ መኾኑንና ጉድለት እንኳን ቢኖር ነገሩ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ቢታይ የሚለው ይገኝበታል። ምርጫው መደረግ አለበት የሚለውንም እምነት የቦርዱ ኃላፊዎች አንጸባርቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ቦርዱ ምርጫው እንዲደረግ ሁሉም የበኩሉን ይሠራል የሚል እምነታቸውን በማንጸባረቅ፣ ቦርዱም የምርጫውን መደረግ አስፈላጊ ነው ብሎ እንደሚያምን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ገልጸዋል። “ሰላም አስፈላጊ ነው፤ በጥይት መካከል እያለፉ ሰዎች ምርጫ ጣቢያ ሔደው ምርጫ ይምረጡ ማለት አንችልም። ግጭት ካለ ቦርዱ ያቀደውንም እቅድ ማስፈጸም አይቻልም” ብለዋል። ነገር ግን ሰላምን የማስፈኑ ሥራ የመንግሥት መኾኑን ጠቅሰው፤ ስለዚህ ይህ ይሆናል በሚል በማመን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አሉ የሚባሉ ችግሮችን በመግለጽና እንዲስተካከሉ በማድረጉ ረገድ ቦርዱ የሚሠራ መኾኑንም ወ/ሪት ብርቱካን ሳይጠቅሱ አላለፉም። ስለዚህ የሁላችንም ኃላፊነት ስላለበት ሁላችንም የበኩላችንን ኃላፊነት መወጣት አለብን የሚሉት ወ/ሪት ብርቱካን፤ ሰላም ማምጣት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችም ኃላፊነት መኾኑን ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

እንዲህ ያሉና ሌሎች አስተያየቶች ቀጣዩ የምርጫ ሒደት በምን መልኩ ለማስተናገድ ስምምነት ላይ ይደረስ ይሆን የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ የምርጫ ቦርድ አቋም ተቆጥሮ በተሠጠኝ ኃላፊነት ልክ እየሠራሁ በመኾኑ የሚጠበቅብኝን አደርጋለሁ የሚል ነው። (ኢዛ)

እንቆቅልሽ የኾነው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ

ጉዳዩ ተፈጸመ ከተባለ ወደ ሁለተኛ ወር እየተጠጋ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታግተዋል የሚለው ዜና የተሰማውም ዘግይቶ ነው። ግን በአገራችን ታሪክ ያልተለመደ ምናልባትም ሊፈጸም ይችላል ተብሎ የማይገመት ቢሆንም፤ የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታግተዋል ተብሏል።

እየተገለጸ ያለው የታገቱት ተማሪዎች ቁጥር የተለያየ ቢሆንም፤ ከታጋቾቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸው። በዚህ የታጋቾችና አጋች ድራማን እንቆቅልሽ ያደገው፤ አጋቹ አለመታወቁ ሲሆን፣ የእገታው ጉዳይን የሚመለከተው መረጃ በየአቅጣጫው ሲስተጋባ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት እየሠጡት ያለው መረጃ የተለያየ ከመኾኑም ባሻጋር፤ “አዎ የታገቱ ነበሩ፤ ከታገቱት ውስጥ 21ዱ ተለቀዋል” ቢባልም፤ ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች ግን ከወላጆቻቸው አልተገናኙም የመባሉ ጉዳይ ሌላ ሊፈታ ያልቻለ እንቆቅልሽ ኾኗል።

ታገቱ ከተባለ በማን? ታግተው ከኾነና ተለቀቁ ከተባሉ ደግሞ የታሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች አሁንም አወንታዊና ተጨባጭ መረጃ ምላሽ የሚሠጥ በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣንም ኾነ መሥሪያ ቤት እስካሁን አልተገኘም። ከዚህም ሌላ አጋቹ እኔ ነኝ በማለት ኃላፊነቱን የወሰድ ቡድንም ኾነ ኃይል በይፋ አልተናገረም። (ኢዛ)

የጎንደሩ ሴራ

የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ በመኾን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ እውቅና የተሠጠው የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ዋዜማ ላይ በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው አንዱ በኾነው በጎንደር በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የነበሩ የጥፋት ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

ቅዳሜ ምሽት ላይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዳስታወቀው በጎንደር የጥምቀት በላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ለማድስ በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት ተይዘዋል ብሏል።

እነዚህ ጥፋቱን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉት ሁለት የጥፋት አባላት የተያዙት ከአራት ኤፍ ዋን ቦምብና ከ200 ጥይቶች ጋር መኾኑም ተገልጿል። (ኢዛ)

መንገድ ዘግቶ ተቃውሞ በትግራይ

ከሰሞኑ ዜናዎች ከሰሜናዊቷ የኢትዮጵያ ክልል ትግራይ በሕንጣሎ ወረዳ ለቀናት የዘለቀው ተቃውሞ ከፍተኛ ትኩረት ካገኙ ክስተቶች አንዱ ነው። አደባባይ የወጣ ተቃውሞ ብዙም የማይሰማበት ትግራይ፤ ከሰሞኑ ግን ከወደ ሕንጣሎ አካባቢ የተሰማው ዜና ነዋሪዎች መንገድ በመዝጋት ይመለሱልን ያሉትን ጥያቄ በአደባባይ ወጥተው መግለጻቸው ነው።

የሕንጣሎ ወረዳ ሕዝብ ተቃውሞ ለቀናት የዘለቀ ሲሆን፣ ለተቃውሞ ያበቃቸው ነባሩ ወረዳ አስተዳደር ይመለስልን በሚል እንደኾነ ተገልጿል።

ሕዝቡ ከመቐለ ሳምረ፣ መቐለ ግጀት፣ መቐለ ሕንጣሎ መስመር መንገድ በመዝጋትና በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞ በማሰማት የሰነበተ ስለመኾኑ፤ በተለይ በዚህ ተቃውሞ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎች አስታውቀዋል። የኣረና ትግራይ አመራር አቶ አምዶም ገብረሥላሴ በፌስቡክ ገጹ ስለሰላማዊ ተቃውሞ ሰልፉ ካሰፈራቸው መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው፤ በደቡብ ምሥራቅ ዞን ኃላፊዎች ሕዝቡን ለማነጋገር ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ ሕዝቡም “ከእናንተ መነጋገር መፍትሔ እንደማይገኝ ያለፉት 6 ወራት ያቀረብንላችሁ አቤቱታዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው። አሁን የቀረን የክልል መንግሥት ምላሽ መስማት ነው” በማለት መልስ መሥጠቱን አስፍሯል። በተያያዘም በወረዳ በክልልና በፌዴራል የወከልናቸው የሕወሓት አባላት ውክልናችንን አንስተናል በማለትም ሕዝቡ መግለጹን አመልክቷል።

ይሄ ጥያቄ የሕንጣሎ ወረዳ ሕዝብ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከ40 በላይ ነባር ወረዳዎች ጥያቄ እንደኾነም አቶ አምዶም አመልክቷል። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብ ውይይትና የመጨረሻው ምዕራፍ

ያሳለፍነው ሳምንት በልዩ ሁኔታ ትኩረት የተሠጠው ዜና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ አሞላል ጋር በተያያዘ ስምምነት ላይ ያልደረሱት የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ ተወያዮች ወደ ዋሽንግተን በማቅናት ያደረጉት ውይይት ውጤት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጠበቅ ነበር። ከዋሽንግተኑ ውይይት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በአዲስ አበባው ውይይት ላይ ግብጽ በግድቡ የውኃ አሞላል ላይ ይዛ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው አዲስ ሐሳብ ውይይቱ ያለውጤት መበተኑ፤ በዋሽንግተኑ ውይይት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎ ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚያስችል ውጤት አይኖረውም የሚለው ሥጋት የብዙዎች ነበር።

ለሦስት ቀናት በዋሽንግተን የተደረገው ድርድር መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ አንዳንዶች ውይይቱ የተጠናቀቀው ግብጽን ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል መልኩ ነው በሚል አስተያየት ሲሠጡ ተደምጠዋል። ይህ መላምት ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፤ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችና የልዑካን ቡድኑ አባላት በዋሽንግተን የሠጡት መግለጫ ግን ሲሠጥ ከነበረው አስተያየት በተቃራኒ ውይይቱ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠበቀ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይ የኢትየጵያ የልዑካን ቡድንን የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሠጡት መግለጫ፤ ግድቡን በተመለከተ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የሚሠጥ ውይይት ፈጽሞ እንዳላደረገች አረጋግጠዋል። ወደፊትም ቢሆን አታደርግም በማለትም ገልጸዋል። የዋሽንግተኑ ውይይት በጥቅል ሲታይና በውይይቱ መደምደሚያ ላይ የተደረሰበት ስምምነት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁንም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

አቶ ገዱና በዋሽንግተን በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ እዚያው ዋሽንግተን በሠጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሦስቱ አገራት ውይይታቸውን ከቋጩ በኋላ የደረሱበት የመግባቢያ ነጥብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሚሠጥ አንዳችም ውይይት ፈጽሞ አለማድረጓን አፅንዖት ሠጥተው ገልጸዋል። ይህም ወደፊትም የኢትዮጵያ ቀዳሚው መርኅ ሆኖ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ፤ በዚህ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮችና ውይይቶች ኢትዮጵያ ሌሎች ግድቦችን የመገንባት መብቷንም የማይጋፋ መኾኑንም ተናግረዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቦች ጋር የማያያዝ ሁኔታ እንዲቀር ማድረግ የተቻለበትን ሁኔታ መፍጠር ስለመቻሉም ተናግረዋል።

የቴክኒክ ውይይቱ ብሎም ከሕግ ጋር የማያያዙት ጉዳዮች አሁንም በዘርፉ ልምድና ክህሎቱ ባላቸው፣ በአገር ፍቅር እንዲሁም በከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ በኾኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተመራ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበት የድርድር ሒደት እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።

በሦስቱ አገራት እየተደረገ ያለው ውይይት ምን ያስገኛል? የሚለው ጉዳይ በዝርዝር የሚቀርብበትና ምናልባትም የመጨረሻ ፊርማ የሚያርፍበትን የስምምነት ሰነድ ይፋ የሚደረግበት ውይይት ከሳምንት በኋላ በዋሽንግተን ይካሔዳል። በሰሞኑ ውይይት ግን መግባባት የተደረሰባቸው አጀንዳዎች ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ ለመሙላት የማይከለክላት መኾኑን አሳይቷል። እንዲያውም በመጪው ክረምት ግድቡን ውኃ መሙላት እንደሚጀምርና ከ4 እስከ 7 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ውኃ የመሙላት ሥራው እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። በዚህ ድርድር መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ያለው መኾኑን ገልጸዋል።

በዋሽንግተን እነአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሠጡት መግለጫ ባሻገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሠጠው መግለጫም፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረገው ቴክኒካዊ ስምምነት በውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ ያተኮረ መኾኑን በማስታወስ፤ የውይይቱ ውጤት ውጤታማ መኾኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ በትብብር ከመሥራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ያሳየና ውጤታማ ስምምነት የተደረገ መኾኑን በዋሽንግተኑ ውይይት ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በኩል የተሠጠው መግለጫ ያመለክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አክለው እንዳመለከቱትም በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በዋሽንግተን የተደረገው ውይይትና መግባባት ላይ የተደረሰበት ነጥብ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠበቀ መኾኑን ነው። የዋሽንግተኑ ውይይትና ውጤቱ ለኢትዮጵያ ያደላ ውጤት የተገኘበት ነው የሚለው የመንግሥት አመለካከትን እንዲጐላ ያደረገው፤ በግብጽ በኩል ይሄ ነው የሚባል መግለጫ አለመሠጠቱ ነው። በተለይ የግብጽ የመገናኛ ብዙኀን በዚህ ጉዳይ ላይ እንደከዚህ ቀደሙ በዝርዝር ያለመዘገባቸው ጉዳይም ሁኔታውን ኢትዮጵያ በተሻለ ውጤት ከማምጣቷ ጋር ያያዙም አሉ። (ኢዛ)

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንቶቹን ከሥራ አገደ

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተፈጠረ ያለው ችግር መሰማት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። አንዱ ጋር ጋብ ሲል ሌላው ጋር የሚነሳውን ግጭት ዘላቂ በኾነ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። በመንግሥት በኩል ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ማድረግ፣ ተማሪዎችን በሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች ማስመከርና የመሳሰሉ እርምጃዎች ተወስዷል። ኾኖም ጥቂቶች በሚለኩሱት እሳት ብዙዎች እየተጐዱ ነው።

ትምህርት የተቋረጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬም አሉ። ሥጋት ያደረባቸውና ለመማር በመቸገራቸው ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ያሉም በርካታ ናቸው። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን የያዘውና የዩኒቨርሲቲዎችን ወቅታዊ ጉዳይ በማጥናት ሪፖርት ያደረገው ኮሚቴ የችግሩ መንሥኤዎችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ ከችግሩ ጋር በተያያዘ እርምጃ የተወሰደባቸውን ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የመምህራንን ቁጥር ከ900 በላይ መድረሱን አመልክቷል። እንዲህ ያሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን፣ አሁንም ለችግሮቹ መንሥኤ ናቸው የተባሉ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችንም ከሥራ እየታገዱ ነው። ሰሞኑንም ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንቶቹን ከሥራ ማገዱ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ ሦስቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች የታገዱት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ መሠረት መኾኑን ተናግረዋል። እነዚህ ሦስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች የመታገዳቸው ዝርዝር ምክንያት ለጊዜው ያልተገለጸ ቢሆንም፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ እንደሚኾን ይታመናል።

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች ከመዛመታቸው ቀደም ብሎ የመማር ማስተማሩ ከተጀመረ ከተወሰነ ሳምንታት በኋላ አንድ ተማሪ የሞተበት መኾኑ አይዘነጋም። (ኢዛ)

ፖሊስና በቁጥጥር ሥር የዋሉት 396 ተጠርጣሪዎች

በአዲስ አበባ በሕገወጥ የጦር መሣሪያ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ የመሬት ወረራ፣ የመኪና ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 390 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ያስታወቀው በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው እነዚህ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ላይም የክስ መዝገብ መከፈቱን አስታውቋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተሠሩ ሥራዎች በጸጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ ትብብር 2 ሺሕ የተለያዩ ሽጉጦችና 18,354 የሽጉጥ ጥይቶች፣ 113 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃና 8,655 የክላሽ ጥይቶች፣ 4 ብሬንና 119 የብሬን ጥይት ተይዟል።

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያን ብርን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ አገራት ገንዘብና ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች መያዛቸው ተገልጿል። በዚህም 8 የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ከሐሰተኛ የብር ኖት ማተሚያ መሣሪያ ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።

በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ ተወስዶ የነበረ 6 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ለመሬት ባንክ ገቢ መደረጉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት አስታውቋል። (ኢዛ)

ኤክሳይዝ ታክስ

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ተካተው ከነበሩ አንቀጾች አንዳንዶቹን እንዲሻሻሉና በረቂቁ እንዲካተቱ መወሰኑ የተገለጸው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ በተሠጠው ማብራሪያ በተለይ በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከ30 በመቶ ወደ አምስት በመቶ እንዲወርድ መደረጉ አንዱ ነው።

ከ1,300 ሲሲ በታች ጉልበት ባላቸው አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ በረቂቁ ላይ የነበረው የ30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ወደ 5 በመቶ መውረዱ የተሽከርካሪዎችን ዋጋ እስከ 83 በመቶ ሊቀንሰው እንደሚችል ተገልጿል።

ማሻሻያ እንዲደረግበት የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ሲጋራንና አልኮል መጠጥን የሚመለከት ነው። በሲጋራና አልኮል መጠጥ ላይ እንዲጣል የቀረበው ሐሳብ አነስተኛ ነው የሚል አስተያየት ከመቅረቡ ጋር ተያይዞ በተደረሰበት ድምዳሜ፤ የመጠጥ ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲጋራ ላይ ብቻ ማስተካከያ እንደሚደረግ ተገልጿል። በዚህም መሠረት በሲጋራ ላይ ተጥሎ የነበረው የ5 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ወደ 36 በመቶ ከፍ እንዲል በማሻሻያው መቅረቡ ታውቋል።

በታሸጉ የውኃ ምርቶች ላይ ሊጣል የነበረው የ15 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ወደ 10 በመቶ ኾኖ በረቂቁ ላይ እንዲካተት መቅረቡንም በዚሁ ጉዳይ ተሠጠው መግለጫ ያመለክታል። አምራቾች የውኃ ፕላስቲኮችን የመሰብሰብና አካባቢን እንዳይበክሉ የማድረግ ሥራ እየሠራን ነው ማለታቸው ለማሻሻያው ምክንያት መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ