የ2012 ዓ.ም. 16ኛ ሳምንት አንኳር ወሬዎች

ከታኅሣሥ 13 - 19 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ
የዓመቱ አሥራ ስድስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች
ኢዛ (ከታኅሣሥ 13 - 19 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ዐይንና ጆሮ ከተሠጣቸው ያሳለፍነው ሳምንት ርዕሰ ዜናዎች በምሥራቅ ጐጃም ዞን በሞጣ በመስጅዶች ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ የተፈጠረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጐላ ብሎ የሚታይ ነው። ጥቃት አድራሾችን መንግሥት ለሕግ ያቅርብልን ከሚሉ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን የያዙ ሠልፈኞች በተለያዩ ከተሞች አደባባይ ወጥተዋል። መንግሥት ጉዳት ለደረሰባቸው መስጅዶችና የንግድ ድርጅቶች ካሣ ሊከፍል እንደሚገባው ያስታወቁበትም ነበር። ለቤተ እምነቶች ጥበቃ እንዲደረግ ጭምር ጥያቄ የቀረበባቸው እነዚህ ሰላማዊ ሠልፎች ከእስልምና እምነት ተከታዮችም የተሳተፉበት ነበር። ሌላው ሰሞናዊ ዜና ብዙ ሲባልባቸው የነበሩት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ለሁለት ቀናት ሲመክሩና የተመረጡ አካባቢዎችን መጐብኘታቸው ነው።
ኤርትራ የራሴ የምትለውን ኤምባሲ አዲስ አበባ ላይ ለመገንባት ቦታ በነፃ እንድታገኝና የግንባታ የመሠረት ድንጋይ በሁለቱ መሪዎችና በከተማዋ ከንቲባ ተቀምጧል። እንዲህ ይፋ ከኾኑ የሁለቱ መሪዎች ክንውኖች ሌላ ምን ተነጋግረው ይሆን? የሚለውም ጥያቄ አመራማሪ ቢኾንም፤ በሳምንቱ ብዙ ከተዘገበባቸው ጉዳዮች አንዱ ይኸው የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ይፋዊ የሁለት ቀናት ጉብኝት ነበር። በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ አዳዲስ ነገሮችን ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ መልእክት ጣል የሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በተሰናዳ እራት ግብዣ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን አይሳካላቸውም ብለው የተናገሩት የሚጠቀስ ነው። ኢሕአዴግ የሚለውና ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የሚታወቀው ፓርቲ ብልጽግና በሚል ስለመካተቱ ማረጋገጫ ይሆናል የተባለው የምርጫ ቦርድ የእውቅና ሠርተፍኬት እንዲሠጥ የተወሰነውም በተጠናቀቀው ሳምንት ነው።
ሳምንቱን በታሪክ ከዚህም በኋላ እንዲታወስ የሚያደርገው የብልጽግና ፓርቲ እውቅና የማግኘት ጉዳይ ትልቅ ፖለቲካዊ ለውጥ ተደርጐ የሚወሰድ ነው። ያሳለፍነው ሳምንት የምናስታውስበት ሌላው ጉዳይ በባሕርያቸውም ሆነ በተመደቡበት የመንግሥት ኃላፊነት በመልካም የሚነሱት የጤና ጥበቃ ዶ/ር አሚር አማን ኃላፊነታቸውን ስለመልቀቃቸው በይፋ በፌስቡክ ገጻቸው የማስፈራቸው ነው። ዶ/ር አሚን ከኃላፊነታቸው ስለመልቀቃቸው መነገር ከጀመረ የሰነባበተ ቢኾንም፤ ባሳለፍነው ሳምንት ግን ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው ወሬ ትክክል እንደነበር አመላክቷል። የስንብት ደብዳቤያቸውም የእርሳቸውን ባሕርይ የሚገልጽ ጨዋነት የተላበሰ እንደነበር የሚያሳይ ስለመኾኑ ብዙዎች አስተያየት የሠጡበት ጉዳይ ነበር።
የሳምንቱ አነጋጋሪ ዜና ተደርጐ የሚወሰደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን በሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂንየነር አዜብ አስናቀ ከሌሎች የቀድሞ ከሜቴክ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በጣምራ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ነው።
የኢንጂንየር አዜብ ከሜቴክ ጋር በተያያዘ ጉዳይ በሙስና መከሰሳቸው ብቻ ሳይሆን፤ በዚህ የክስ መዝገብ ስማቸው ከተዘረዘሩት ተከሳሾች ውስጥ ኢንጂንየነር አዜብን ጨምሮ አንዳንዶቹ በአገር የሉም የሚለው ወሬ ነው። ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ይካሔዳል ወይስ አይካሔድም? የሚለው ጥያቄ አሁንም ብዙዎች ቁርጥ ያለ ምላሽ ለመሥጠት የሚቸገሩበት ቢኾንም፤ ከሰሞኑ በተከታታይ ከምርጫ ቦርድ የሚወጡ ዜናዎች ግን ምርጫውን ለማካሔድ እየሠራና እየተዘጋጀ መኾኑን የሚያመላክቱ ናቸው።
በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዙሪያ ወቅታዊው አጀንዳ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ይህንን ረቂቅ አዋጅ ተንተርሰው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ዘገባዎች የተስተናገዱ ሲሆን፣ በተለይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የሚያስመጡ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጁ ሊፈጥር ይችላል ያሉትን ሲገልጹ ሰንብተዋል። ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ 500 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ሲጣል ነው መባሉን ብዙዎች ተገቢ አይደለም በሚል እየተቹት ነው። ነገር ግን የታክሱ መልካም እድል አልታየም የሚሉ አሉ። እነዚህንና በሌሎች ሳምንታዊ ዐበይት ክንውኖች ዙሪያ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ከተለያዩ ምልከታዎች አንፃር የተጠናከሩት ዘገባዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።
በሞጣ መስጅዶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ያስነሳው ተቃውሞ
ከሁለት ሳምንታት በፊት በምሥራቅ ጐጃም ዞን ሞጣ ከተማ ውስጥ ይፈጠራል ተብሎ ያልታሰበ ክስተት ታየ። እስካሁን ጥርት ያለ መረጃ ያልተገኘለት ጥቃት ግን በሦስት መስጅዶችን በእሳት ለብልቧል። በአንድ ቤተክርስቲያን ላይም ተሞከረ የተባለው ጥቃት ንብረት ወድሟል። ከቤተ እምነቶች ውጭ በንግድ ተቋማት ላይም የደረሰ ቃጠሎ ነበር። በሞጣ የደረሰው አደጋ እንደተሰማ ወዲያው ድርጊቱን በማውገዝ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የቀደመ አልነበረም። ባልተለመደ ሁኔታም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማና የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ተመሳሳይ መልእክት ያለውን ውግዘት በፌስቡክ ገጾቻቸው አስነብበዋል።
የእነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት ውግዘት ከዚህ ቀደም ብዙ ያልተለመደ ቢኾንም ወዲያው ድርጊቱን የሚያወግዙ መልእክቶች ከየቦታው ተሰምተዋል። የሃይማኖት ተቋማት መግለጫ አውጥተዋል። የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ድርጊቱን በማውገዝ ብቻ ሳይወሰን በድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በማሰስ ከ33 በላይ ተጠርጣሪዎችን መያዙን አስታውቋል።
በሞጣው ድርጊት በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ድርጊቱ ለምን ኾነ? በማለት ጥያቄው በአግባቡ መልስ ማግኘት አለበት በሚል ከየአቅጣጫቸው ተቃውሞን ቀስቅሷል። የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ ይቅረቡ የሚል ድምፅ የተሰማባቸውና ሌሎች መልእክቶችን የያዙ መፈክሮችን በመያዝ፤ በተለይ ባሳለፍነው ዓርብ በተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሒደዋል። እነዚህ ሰላማዊ ሠልፎች በአንዳንድ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች በተለይ ባሌ፣ ኢሊባቡር፣ አርሲና ሌሎች ከተሞች ሰልፎች ተካሒደዋል።
በአማራ ክልልም እንደ ደሴ፣ ወልድያ፣ መርሳና የመሳሰሉ ከተሞች ላይ ድርጊቱን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምንም ዐይነት የተጠራ ሰልፍ ያለመኖሩን ቢያሳውቅም፤ በእነዚህ ከተሞች በመስጅዶች ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም በተካሔዱት ሰልፎች ላይ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ እንዲያቀርብ፣ የተጐዱ የእምነት ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች መልሰው እንዲገነቡ እንዲያደርግና ካሣ እንዲከፈል ጥያቄ የቀረበባቸው ነበር። በአዲስ አበባም በአንዳንድ መስጅዶች ውስጥ ተመሳሳይ መልእክት በማሰማት የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቷል።
ዓርብ ታኅሣሥ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. የእስልምና እምነት ተከታዮች ሰልፍ እንዲያካሒዱ ተጠርቷል በማለት የተፈጠረ ውዝግብም ነበር። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ግን ይህ ተጠራ የሚባለው ሰላማዊ ሰልፍ ከጠቅላይ ምክር ቤቱ እውቅና ውጪ መኾኑ ተገልጿል። የምክር ቤቱ ጸሐፊ ሐጂ ሼሕ ቃሲም ታጁዲን ጉዳዩን አስመልክተው በሠጡት መግለጫ፣ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ተጠራ የተባለው ሰልፍ ከምክር ቤቱ እውቅና ውጪ መኾኑን አስታውቀዋል። ስለኾነም ሕዝበ ሙስሊሙ ሰላማዊ ሰልፉ ተጠራ በተባለበት ቀን የሶላት ሥነ ሥርዓቱን እንደ ከዚህ ቀደሙ በተረጋጋ መልኩ እንዲያከናውን አሳስበዋል። በምዕመናን የእስልምና አስተምህሮ በመተግበር ለዘመናት የዘለቀውን የመቻቻል ባህል ሊጠብቁ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች መሰል ጥፋቶችን በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት ለመክፈል የሚስተዋለውን ሁኔታ በቅንጅት ማስወገድ እንደሚገባቸውም ጥሪ አቅርበዋል። ይህ መግለጫ ቢወጣም በጁምዓ ዕለት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቃውሞ ድምፅ የተሰማ ሲሆን፤ ምዕመኑም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን ያስተጋባበት ነበር።
አንዳንድ የሰላማዊ ሰልፎችም ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በጋራ በመኾን የተደረገ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን ይጠብቅ የሚሉ መፈክሮችን የያዙ፣ የመንግሥት ቸልተኝነትን ያወገዙ ሰላማዊ ሰልፎችም ናቸው። ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖት ደሴት ናት፣ የሚዲያዎች የሃይማኖት መድሎ ይቁም ሁሉም ቤተእምነቶች ይጠበቁ የሚሉ መፈክሮች ሁሉ ታይተዋል። (ኢዛ)
የኢሕአዴግ ፋይል ሲዘጋ
ከሳምንቱ ዐቢይ የፖለቲካ ዜናዎች የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ብልጽግና ፓርቲ ያቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ በማጽደቅ ውሳኔ ማሳለፉ ነው። ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ፓርቲዎች ራሳቸውን አክስመው በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ራሳቸውን በማኖር አዲሱን ፓርቲ መሥርተዋል። ይህም ኢሕአዴግ የሚለውን ባርኔጣቸውን አውልቀው ብልጽግና የሚባለውን ፓርቲ ባርኔጣ ለማድረግ ስምምነት ላይ የደረሱበትን ድምዳሜና በዚሁ ድምዳሜ መሠረት የብልጽግና ፓርቲ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጠውን የምዝገባ ጥያቄ ቦርዱ ተቀብሏል።
ይህም ኢሕአዴግ የሚለው ስያሜ ያበቃለት መኾኑንና በዚያ ምትክም ብልጽግና መተካቱን ያሳየ ትልቅ የፖለቲካ ክንውን ተደርጐ ተወስዷል።
አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፤ ቦርዱ ጥያቄውን ከመረመረና ለፓርቲ ምዝገባው ሊሟሉ የሚገባቸውን ቦርዱ ካረጋገጠ በኋላ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (የእውቅና ሰርቲፊኬት (የምሥክር ወረቀት)) ለብልጽግና ፓርቲ እንዲሠጠው መወሰኑ ታውቋል።
ስምንቱ ፓርቲዎች በየፊናቸው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን በማካሔድ በደረሱበት ውሳኔ መሠረት ውሕደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም፣ እንዲሁም ውሕደቱን ለመመሥረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ሕጉን ተከትሎ የተፈጸመ እንደኾነም ተገልጿል። በመኾኑም ስምንቱም ፓርቲዎች እስካሁን የሚታወቁበትን ፓርቲዎች በመሰረዝ ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሠጠው ተደርጓል።
በመኾኑም ውሕዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሠረት በተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ውሕደቱ ያስገኘውን ሀብት፣ ንብረትና ዕዳ የሚያሳይ የሒሳብ ሪፖርት ለቦርዱ እንዲያቀርብም ቦርዱ መወሰኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚሁ መሠረት ሀብትና ዕዳን በተመለከተው መረጃ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ አስቀምጧል።
ብልጽግና ፓርቲን ተዋሕደው የመሠረቱት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያንዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ሕዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋሕአዴን) እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉሕዴፓ) ናቸው። ሆኖም የፓርቲው አመሠራረት ፕሮግራም የሚቀበሉ ፓርቲዎችም ኾኑ ግለሰቦች እንዲካተቱበት የሚፈቅድ በመኾኑ ብልጽናግ ተጨማሪ አባላትን እየቀላቀለ ይሔዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የብልጽግና አመሠራረትና ሒደት ሕጋዊ መኾኑን ተከትሎ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ብልጽግና ፓርቲ ከአባላቱ ጋር በብልጽግና ፓርቲ ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው።
ይህ እውቅና ደግሞ የኢሕአዴግን ስም በማክሰም ብቻ ወይም ስያሜ በመለወጥ ብቻ የኾነ አይደለም። ፓርቲው ከቀደመው የኢሕአዴግ አካሔድ በተለየ ሊሔድ የሚችልባቸው ብዙ ነገሮች ያሉት መኾኑን በማሳየት፤ በብልጽግና ፓርቲ ዙሪያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውይይት እየተደረገ ነው። ሕወሓትን ያላካተተው የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ አሁን ደግሞ ሕጋዊ ወደመኾን መሸጋገርን ተከትሎ አንዳንድ የሕወሓት አባላት ወደ ብልጽግና ፓርቲ ለመቀላቀል እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም ባለፈው ሳምንት ከተሰሙ ዜናዎች አንዱ ነበር። ይሁን እንጂ በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ዓርብና ቅዳሜ በመቀሌ በሕወሓት በተጠራ የውይይት መድረክ ላይ ዶ/ር ደብረጽዮን አንዳንድ ለሥልጣን ብለው ያልተገባ ሥራ የሚሠሩ ያሉዋቸውን የክልሉን ተወላጆች የሚያስጠነቅቅ መልእክት ማስተላለፋቸው አነጋጋሪ ኾኗል። እንዲያውም እርምጃ እንወስድባቸዋለን እስከማለት ደርሰዋል። (ኢዛ)
የጤና ሚኒስትሩ ስንብትና የትምህርት ሚኒስትሩ መከተል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም እጩ ከሾሙዋቸው 16 የካቢኔ አባላት ውስጥ አንዱ የነበሩት ዶክተር አሚር አማን ከሥልጣን መልቀቃቸው እውን ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከሾሟቸው ሚኒስትሮች ዶ/ር አሚን ሥልጣናቸውን በመልቀቅ የመጀመሪያው ኾነዋል።
በመልካም ሥነ ምግባራቸውና በኃላፊነት በቆዩባቸው ወቅቶች በበጐ የሚነሱት ዶ/ር አሚን ከሥራ የለቀቁበትን ምክንያት ባይገልጹም። በፌስቡክ ገጻቸው የስንብት ደብዳቤያቸው ግን የሚከተለውን ይመስላል፤ “በቅድሚያ አገሬንና ሕዝቤን በጤና ሚኒስትርነት እንዳገለግል ለሠጡኝ እድል፣ የተሰጠኝን ኃላፊነት ማሳካት እንድችል ላሳዩኝ ያላሰለሰ ድጋፍና ጽኑ እምነት እንዲሁም ያቀረብኩትን የሥራ መልቀቂያ ስለተቀበሉኝ ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ከልብ አመሰግናለሁ።
“በጤና ሚኒስቴር በተለያዩ ኃላፊነቶች የቆየሁባቸው ዘጠኝ ዓመታት፣ በተለይም ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኒስትርነት ባገለገልኩባቸው አንድ ዓመት ከስምንት ወር በፍጹም መከባበርና ለሥራ ቅድሚያ በመሥጠት በጋራ ስላከናወናቸው ተግባራት የሥራ ባልደረቦቼን፣ ጓደኞቼንና የልማት አጋር ድርጅቶችን በሙሉ በእጅጉ ማመስገን እወዳለሁ። በእነዚህ ዓመታት የተቀዳጀናቸው ስኬቶች ሁሉ የጋራ ጥረት ውጤቶች እንደመኾናቸው በእኩል ልንኩራራባቸው ይገባል። ያላሟላናቸው ነገሮችን በቀጣይ ትኩረት ሠጥቶ በመሥራት ወደ ስኬት እንደሚመጡ እርግጠኛ ነኝ።
“ገና በወጣትነት ዕድሜ የሕክምና ትምህርቴን ጨርሼ ሥራ ከጀመርኩበት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በሙያዬና በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት ዘርፎች ሳገለግል ያለኝን እውቀት፣ ጉልበትና የሥራ ልምድ ሳልሰስት ደስ ብሎኝ በሥራ ላይ ለማዋል ጥሬያለሁ። አሁን ወደ ኋላ ስመለከተው ግን በቆይታዬ ወቅት ከሠራሁት ይልቅ የተማርኩት፣ ከሠጠሁትም የተቀበልኩት እጅግ የላቀ እንደሆነ ተረድቻለሁ። “ተማሪ ካስተዋለ፤ አስተማሪ ሁልጊዜ አለ” እንዲሉ፤ ጥሩ ሥሠራ በማበረታታት፤ ሳጠፋም በማረም የዛሬ ማንነቴን በመቅረጽ በማንነቴ ላይ የማይጠፋ አሻራውን ላስቀመጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንደበቴ ከማመስገን በተጨማሪ በቀጣይ የሥራ ዘመኔ ሁሉ አቅሜ በፈቀደ መጠን አገሬንና ያደኩበትን ቤቴን የጤና ሚኒስቴርን ለመደገፍ ቃል እገባለሁ!” የሚል ነበር።
የዶ/ር አሚን ከሥልጣን የመልቀቅ ጉዳይ ወራት የተቆጠሩ ቢኾንም ይህንን አረጋጋጭ የኾነ መረጃ ሳይቀርብ ቆይቷል። እርሳቸውም ሥራቸውን ሲሠሩ ቆይተው ታህሳስ 14 ቀን ግን በራሳቸው የፌስቡክ ገጽ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን አሳውቀዋል።
ዶ/ር አሚን ተወልደው ያደጉት ባህርዳር ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት በሕክምና ሳይንስ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪ በሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ሳይንስ አግኝተዋል። በሥራው ዓለም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ዕቅድና ፋይናንስ ዳይሬክተር ጄነራል፤ በኦሮሚያ ክልል በሊሙ ገነት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፤ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታና በመጨረሻም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመኾን አገልግለዋል።
ይህ ዜና በተሰማበት ሳምንት መጨረሻ ላይ ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ የሥራ መልቀቂያ አስገብተው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ታውቋል። ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ የሥራ መልቀቂያውን ያስገቡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በሚገኘው ዩኔስኮ ውስጥ ለመሥራት እንደኾነ እየተነገረ ነው። (ኢዛ)
ኢንጅነሯና በሜቴክ ኃላፊዎች ላይ የቀረበ የ5.1 ቢሊዮን ብር ክስ
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በርካታ የተፋለሱ ተግባራትን ፈጽሟል በሚል ተወቃሽ በመኾን በተደጋጋሚ ስሙ ሲነሳ የቆየው ሜቴክ አሁንም ድርጅቱን ይመሩ የነበሩ ግለሰቦች አዳዲስ ክሶች እየቀረቡባቸው ነው። ከሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ሌላ የሌሎች ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን እየነካካ ስለመኾኑ በዚህ ሳምንት በቀድሞዋ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ ላይ የተመሠረተው ክስ ተጠቃሽ ነው።
ኢንጂንየር አዜብ ከቀድሞ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተያይዞ የተመሠረተባቸው ክስ፤ ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ተካሒዷል በተባለ የደን ምንጣሮ የሥራ ውል ጋር የተያያዘ ነው። ስለተመሠረተው ክስ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተሠጠው ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ የሚያርፍበትን 123 ሺሕ 189 ሔክታር ስፋት የሪዘርቬየር ክሉሪንግና ባዮማስ ዝግጅት ሥራ ደኖችን የመመንጠር፣ የማጽዳትና ከአካባቢው (ከግድቡ አርቆ) ወደተዘጋጀለት ቦታ የማጓጓዝ ሥራን ለመሥራት ከሜቴክ ጋር የተደረገው ውል ለመንግሥትና ለሕዝብ ሀብት ብክነት ምክንያት በመኾኑ ነው።
እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መረጃ በዚህ ውል የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በ5.15 ቢሊዮን ብር ሥራውን ለማከናወን በተዋዋሉት ውል መሠረት ሥራው መጠናቀቅ በሚገባው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግሥት ገንዘብ እንዲባክንና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመኾኑ ክሱ መመስረቱን ያመለክታል። በመኾኑም ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመኾን ተከሳሾች በፈጸሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል፣ አንዳንዶቹ የማይገባ ጥቅም ለራሳቸው ለማገኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብና ኃላፊነታቸውን በመጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ስለመከሰሳቸው ያመለክታል።
ኢንጂንየር አዜብ አስናቀ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪከ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚነት የተነሱ መኾኑ ይታወሳል። ይህ ክስ የተመሠረተውም ኢንጂንየር አዜብንና የቀድሞ የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤልን ጨምሮ 50 ሰዎች በሚገኙበት የክስ መዝገብ ነው። ክሱ በተመሠረተበት ወቅት ግን ኢንጂንየር አዜብን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ እንደኾነም ተነግሯል። (ኢዛ)
የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅና የተምታቱ ጉዳዮች
በሳምንቱ አነጋጋሪ ከኾኑ ጉዳዮች መካከል መንግሥት ኤክሳይዝ ታክስን አዋጅ ለማሻሻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዲስ ረቂቅ አዋጅ ነው። መንግሥት ይህንን አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት ጠቀሜታነቱን በማጉላት ጠቅሶታል።
ይህ ኤክሳይዝ ታክስ በረቂቁ ላይ በተመለከተው መሠት የሚጸድቅ ከኾነ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አሁን በገበያ ላይ ከሚሸጡበት ዋጋ ሁለትና ሦስት እጅ ብልጫ እንዲሸጡ የሚያስገድድ እንደኾነም እየተገለጸ ነው።
ኤክሳይዝ ታክስ ለምን እንደሚጣል ከሚያስገነዝቡ መረጃዎች መረዳት እንደሚቻለው የቅንጦትና መሠረታዊ በመኾናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጐታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጐዱና ማኅበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ነው። ታክሱ የገቢ መሰብሰቢያ መሣሪያ በመኾን ጭምር ያገለግላል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ለተጨማሪ ውይይት ረቂቁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይገኛል። በረቂቁ ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ውይይት ሲደረግበት አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም በአንዳንድ ምርቶች ላይ በተለይም ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው ኤክሳይዝ በዛ የሚል ይገኝበታል።
ከፓርላማው ውጭም በዚህ ኤክሳይዝ ረቂቅ አዋጅ ላይ በብርቱ ያሟገተው ይኸው በአገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እስከ 500 በመቶ የሚደርስ የኤክሳይዝ ታክስ መጠን የተጋነነ ሆኗል የሚል ነው።
እስካሁን ሥራ ላይ ያለው ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ፤ ኤክሳይዝ ታክስ የሚሰበሰብባቸው ዕቃዎች በ19 ምድብ የተደለደሉ ሲሆን፣ ከዕቃዎቹ የሚገኘውን ታክስ ለመሰብሰብ ባለሥልጣኑ (የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን) የሚገለገልበት አነስተኛው ምጣኔ ወይም የማስከፈያ ልክ አነስተኛው 10 በመቶ ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ 100 በመቶ እንደሆነ ያመለክታል። በዚሁ በቀደመው አዋጅ የኤክሳይዝ ታክስን ምጣኔዎች አሥር ናቸው። እነሱም 10፣ 20፣ 30፣ 33፣ 40፣ 50፣ 60፣ 75፣ 80 እና 100 በመቶ የሚጣልባቸው ናቸው። እነዚህ ምጣኔዎች ሊከፈል የሚገባውን የኤክሳይዝ ታክስ ለማስላት ያገለግላሉ። በቀደመው አዋጅ ከፍተኛ የሚባለው የ100 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ደግሞ ተሽከርካሪዎች ናቸው።
እስካሁን ባለው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለውን ኤክሳይዝ ታክስ እንዲህ ባለው መንገድ ያስቀምጠዋል። ለመንገደኞች መጓጓዣ የሚኾኑ ተሽከርካሪዎች (አውቶሞንበሎች) “እስቴሽን ዋገን” የአገልግሎት መኪናዎች ላንድሮቨሮች፣ ጂፖች፣ ፒክአፖች እና እነዚህንም የመሳሰሉ ተሽከርካሪዎች፣ ባለሞተር ካራቫኖች ጭምር የተገጣጠሙ ወይም ያልተገጠሙ በመጀመሪያ ሲመጡ ሊኖራቸው ከሚገባው መሣሪያ ጋር እስከ 1,300 ሲ.ሲ 30 በመቶ፤ ከ1,301 ሲ.ሲ በላይ እስከ 1,800 ሲ.ሲ ላላቸው ደግሞ 60 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣላል። ከ1,800 ሲ.ሲ. በላይ ለኾኑ ተሽከርካሪዎች 100 በመቶ ኤክሳይዝ እንደሚከፈልበት ያሳያል። በአዲሱ ረቂቅ ላይ ግን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከውጭ የሚገቡ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ግን ከአንድ መቶ እስከ 500 በመቶ ታክስ የሚጥል መኾኑን ነው። ይህም የኤክሳይዝ ታክስ አጣጣል በየተሽከርካሪዎቹ ዕድሜ ላይ ተንተርሶ የሚሰላ መኾኑን ረቂቅ ሕጉ ያሳያል። ይህ ማለት ቀድሞ ከፍተኛነት የሚባለው የ100 በመቶ የኤክሳይዝ መጠን በአዲሱ አዋጅ 100 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ክፍያ መነሻ መኾኑን ነው።
በዚህ ስሌት መሠረት አንድ ከውጭ የሚገባ ከዜሮ እስከ አንድ ዓመት ዕድሜ ያለው ወይም ወደ አገር ከመግባቱ በፊት እስከ አንድ ዓመት አገልግሎት የሠጠ ከኾነ የሚታሰብበት የኤክሳይስ ታክስ 100 በመቶ ነው። ከሁለት ዓመት እስከ አራት ዓመት አገልግሎት የሠጠው ላይ ደግሞ 200 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ይታሰብበታል። እንዲህ እያለ የአገልግሎት ዘመኑ በጨመረ ቁጥር የኤክሳይዝ መጠኑ እየጨመረ ሄዶ፤ ከአራት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት አገልግሎት የሠጡ ተሽከርካሪዎች 300 በመቶ፣ ከሰሳት ዓመት በላይ የኾኑት ላይ ደግሞ 500 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣልባቸው እንደኾነ ረቂቁ ያሳያል። በቀድሞውና በረቂቁ ኤክሳይዝ ታክስ መካከል መሠረታዊ ልዩነቱ የቀድሞው ለአሮጌውም ለአዲሱም ተመሳሳይ ታክስ መጣሉ ነው። አዲሱ ግን በመለያየት ያስቀምጣል።
በቀድሞ የኤክሳይዝ ታክስ ሕግ አንፃር ሲታይ በእርግጥም ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሊጣል የታሰበው ኤክሳይዝ ታክስ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በአሁኑ ወቅት በሰፊው መነጋገሪያ የኾነው የዚህ ታክስ ጉዳይ ትኩረት ሊስብ የቻለው ከአዲስ ተሽከርካሪዎች ይልቅ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ገበያውን የያዙት በመኾኑ ነው።
ኤክሳይዝ ታክስ ለአገሪቱ አዲስ ባይኾንም አሁን ሥራ ላይ ያለው ኤክሳይዝ ታክስ ሕግን በአግባቡ ካለመተግበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ብዥታ ስለመኾኑም የሚናገሩ አሉ። እስካሁን ባለው የኤክሳይዝ ታክስ ሕግ መሠረት 19 ምርቶች ተፈጻሚ ይኾንባቸዋል።
ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ካገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ከተጣለው ታክስ ሌላ በሌሎች ምርቶች ላይ የተደረገው ጭማሪ ከቀደመው ጋር ብዙም ልዩነት የሌለው፤ በአንዳንድ ምርቶች ላይም ቅናሽ የተደረገበት ነው።
በአዲሱ ረቂቅ የኤክሳይዝ ታክስ ቅናሽ ከተደረገባቸው ውስጥ ደግሞ አንዱ ስኳር ነው። ይህ ምርት በቀደመው አዋጅ 33 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጠየቅበት የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ወደ 20 እና 30 በመቶ ወርዷል። እንደ ዘይት ያሉ ምርቶች በአዲሱ ረቂቅ እንደ ይዘታቸው መጠን ከ30-50 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸዋል። በቀደመው አዋጅ ለስላሳ መጠጦች 40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸው የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ረቂቅ ደግሞ እነዚህ ምርቶች 30 በመቶ ሆኗል። በቀድሞ ረቂቅ እንደ ቢራ፣ ውስና የወይን ጠጅ ምርቶች 50 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ረቂቅ ደግሞ እነዚህ ምርቶች 80 በመቶ ሊጣልባቸው እንደሚገባ ረቂቁ ያሳያል።
ከተሽከርካሪዎችና ከአንዳንድ ምርቶች ውጭ በቀድሞ አዋጅ ኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ምርቶች ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ በአብዛኛው ተቀራራቢ ነው። አዲሱን ረቂቅ ከቀደመው በተለየ የሚያሳየው ግን እንደ መኪና ያሉ ምርቶች ላይ ከአምስት እጅ በላይ ጭማሪ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፤ በ19 ተወስነው የነበሩ ምርቶች መጨመራቸው ነው። በአዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዳዲስ ምርቶች ተካተው ኤክሳይዝ ታክስ እንዲከፈልባቸው ተደርጓል። ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልባቸው ተብለው በአዲሱ ረቂቅ ከተካተቱት ምርቶች ውስጥ ጨው፣ ዘይት፣ ርችቶች፣ የፕላስቲክ ከረጢት ፌስታል፣ ሒውማን ሔር፣ ሞተር ሳይክልና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
የዚህ ረቂቅ ገና በምክር ቤት የሚመከርበት ቢኾንም፤ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ገና ከወዲሁ ዋጋቸው እስከ እጥፍ የሚደርስ ዋጋ እየተጠየቀባቸው እንደኾነ እየተነገረ ነው።
ሕጉ ሳይጸድቅ ገና ከወዲሁ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ዋጋን ለማስወደድ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ እንዲንጸባረቅ እየተደረገ ሲሆን፣ ሒደቱ ከገበያ ሥርዓት ውጭ መኾኑን የሚገልጹ አሉ።
በዚህ ደረጃ ግብይት ሊፈጸም ይችላል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ። አሁን እየተጣራ ያለው ዋጋ የተጋነነ መኾኑን የሚገልጹ ደግሞ፤ “የሚሰማው ዋጋ እኮ አዲስ መኪና ያስገዛል” በማለት ሁኔታውን ውዥንብር ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው የሚል ነው። አስተያየቶቹ የተዘበራረቁ ቢኾኑም አዲሱ አዋጅ አሁን ባለው መንገድ ቢጸድቅ እንኳን ዋጋ ጭማሪ ሊኖር የሚገባው ከዚህ በኋላ ሊመጡ በሚችሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ነው እንጂ በገበያ ላይ ባሉት ላይ አይደለም በሚል የሚሞግቱ አሉ።
የዚህ ረቂቅ ገና በምክር ቤት የሚመከርበት ቢኾንም፤ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ገና ከወዲሁ ዋጋቸው እስከ እጥፍ የሚደርስ ዋጋ እየተጠየቀባቸው እንደኾነ እየተነገረ የመኾኑ ጉዳይ አነጋጋሪ ሲሆን፤ ረቂቁ ይዞ የመጣውን መልካም እድል ያለመመልከት ችግር እንዳለ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች የሚገለጹ አስተያየቶችን የሚተቹም አሉ። የአሮጌ ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ጐልቶ የመውጣቱን ያህል፤ ለአዲስ መኪኖች የተሠጠውን እድል ያለመመልከት ችግር ታይቷል።
ነገር ግን በዚህ አዋጅ ታክስ በመጫን አሮጌ ተሽከርካሪዎች ገበያ ውስጥ የያዙትን ስፍራ ሲለቁ ሕብረተሰቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ምን ይደረጋል? የሚለው ጥያቄን ይመልሳል በማለት ይሞግታሉ። አሁን ትልቅ ችግር የኾነው መኪና ለመሸመት የሚወጣ ገበያተኛ፤ መኪናው እያለ ሊሸጥለት አለመቻሉ ነው። አንዳንዶች ሕጉ እስኪለይለት አንሸጥም በሚል ይዘውታል። ይህ ግን ፈጽሞ አግባብ እንዳልኾነ የሚሞግቱ ወገኖች፤ አዲሱን ረቂቅ በደንብ ካለመገንዘብ የተፈጠረ ክፍተት እንዳለ ያሳያል።
በዚህ ረቂቅ ሕግ መሠረት ለሁሉም ተሽከርካሪዎች ዐይነት አዲስ ከኾነ እስከ 30 በመቶ ብቻ ኤክሳይዝ ይከፈልበታል። እንዲያውም አንዳንድ 16 ሰዎች የማይዙ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እስከ አራት ዓመት ቢያገለግሉ እንኳን ኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈልበት ከ30-100 በመቶ ነው። ይህም ከቀደመው ያነሰ ኤክሳይዝ የሚከፈልበት መኾኑን የሚያሳይ በመኾኑ አስፈላጊ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው ሊቀንስ ይችላል እንጂ የሚጨምርበት ምንም ምክንያት የለም።
ሌላው በዚህ ረቂቅ ላይ እንደ መልካም የሚታየው በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች የሚጣልባቸው ኤክሳይዝ ታክስ 30 በመቶ የሚከፈልባቸው በመኾኑ አዲሱ ረቂቅ እንደታሰበው የተሽከርካሪ ዋጋን የማያስወድድ መኾኑን ነው። በመኾኑም ከሰሞኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተሽከርካሪን ሊያስወድድ ይችላል በሚል የሚቀርበው አስተያየት ፈጽሞ ትክክል ያለመኾኑንና ረቂቁን በሚገባ ካለመመልከት የመነጨ እንደኾነም የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገርቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገልጸዋል። ስለዚህ ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ላይ እስከ 500 በመቶ ታክስ መጣሉን በማጋነን የሚቀርበው ነገር ትክክል እንዳልኾነ ይጠቅሳሉ። ሲያስፈልግ ለእነዚህ ዕቃዎች ማምረቻ የዋሉ ግብዓቶች ወደ አገር ሲገቡ የተከፈለው የኤክሳይዝ ታክስ ተቀናሽ ይደረጋል።
እነዚሁ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ እንደገለጹት ከኾነ፤ “ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት መኪኖች ውስጥ 88 በመቶ የሚኾኑት ያገለገሉ መኾናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ አንጻር ያገለገሉ መኪኖችን ለመጠገን፣ እንዲሁም መለዋወጫ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አገሪቷ ታባክናለች” በማለት አስተያየታቸውን ሠጥተዋል። (ኢዛ)
ተከታታይ እውቅናዎች
ኅዳርና ታኅሣሥ 2012 በተለየ የሚታዩበት ያደረጋቸው አንድ ክስተት የታየበት ወር ነው ማለት ይቻላል። ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ታዋቂ የመገናኛ ብዙኀን እውቅና ያገኙበት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ወር የኖቤል ተሸላሚ ከኾኑ በኋላ ሰሞኑን ይፋ የኾነው የፋይናንሽያል ታይምስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣ ከፈረንጆቹ 2010 – 2019 በነበሩት 10 ዓመታት በዓለም ላይ ለውጥ በማምጣት ከተጠቀሱት 50 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ዝርዝር ስለመካተታቸው ይፋ የኾነው ባለፈው ሳምንት ነበር። በፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣ በፖለቲካው ዘርፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አንዱ አድርጐ ከጠቀሰበት ዘርፍ በተፅዕኖ ፈጣሪነት ከጠቀሳቸው የዓለም መሪዎች ውስጥ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን፣ ቱኒዚያዊው ሞሐመድ ቡአዚዝ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመን መራሂት መንግሥት አንጄላ ሜሪልል፣ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቻይናው መሪ ዢዥንፒንግ ተካተውበታል።
ከባለፈው ሳምንት የፋይናንሽያል ታይምስ ምርጫ ቀደም ብሎ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በፎርቢስ መጽሔት የ2019 ከዓለም 100 ሴት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አንዷ አድርጓቸዋል። ሲኤንኤን ደግሞ ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብራቱን የዓመቱ ጀግና በማለት መምረጡ ይታወሳል። ወ/ሮ ፍሬወይኒ በሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ በማምረት በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ምክንያት በሚያጋጥማቸው የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ በማድረግ ለዓመታት በሠሩት በጐ ተግባር ነው። አሕመድ ሽዴ ደግሞ ምርጥ የገንዘብ ሚኒስቴር በመባል ተመርጠዋል። (ኢዛ)
ደሃይቱ ተበዝባዥ አገር ኢትዮጵያ
- በአስር ዓመት ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተመዝብራለች
ደሃይቱ አገር ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ፣ በሙስናና በሌሎች ተያያዥ የሌብነት ተግባራት በየዓመቱ የምታጣው ሀብትና ገንዘብ፤ ይቺ አገር እውን ደሃ ናት ወይ? የሚያስብል ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀን በማስመልከት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ የቀረበ አንድ ጥናት የዚችን አገር ብዝበዛ ምን ያህል የከፋ እንደኾነ የሚያሳይ ነው። ይኸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2010 ድረስ ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብቷ መመዝበሩን የሚገልጽ ነው። በመረጃው እንደተመለከተው ሙስና ዓለማችንን በየዓመቱ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ገቢ 5 በመቶ እያሳጣት ሲሆን፤ አፍሪካም ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሙስና የሚዘረፍባት አህጉር ሆናለች። (ኢዛ)
የምርጫ ዝግጅት
- ቦርዱ የምርጫ ሰሌዳውን ይፋ አደርጋለሁ ብሏል
የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ከግምት ያስገቡ የፖለቲካ ምሁራን ምርጫው ይራዘም የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ሁሉ፤ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲና ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ ምርጫው እንደሚካሔድ እየገለጹ ነው። ነገር ግን በአንዳንዶች ዘንድ ምርጫው መደረጉ ባለየለት ሰዓት፣ እንዲሁም ሊካሔድ ይችላል የሚል አመለካከቶች የሚያንጸባርቁ ያሉ ቢኾንም፤ ምርጫ ቦርድ ግን ከእሱም የሚያሠራጫቸው መረጃዎች ለምርጫው አስፈላጊ የኾኑ ዝግጅቶች እያደረገ መኾኑን ነው።
በተለይም በቅርቡ ከቦርዱ የወጣው መረጃ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሔድ ቁርጠኛ መኾኑንና ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እያከናወንኩ ነው ብሏል። በቅርቡም የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል። (ኢዛ)
ዘመን ባንክ ከ2010 የበጀት ዓመት 86 በመቶ በላይ አተረፈ
ከሰሞኑ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ካቀረቡት ባንኮች መካከል አንዱ ዘመን ባንክ ነው። ዘመን ባንክ ከሌሎች ባንኮች በተለየ አነስተኛ የቅርንጫፍ ቁጥሮች ያሉት ነው። ባንኩ ሲመሠረት ቅርንጫፎች ለማስፋፋት ያላቀደ የነበረ ሲሆን፣ በብሔራዊ ባንክ አስገዳጅነት ባለፉት አራት ዓመታት 43 ቅርንጫፎችን መክፈቱ ይታወቃል።
በ2011 የበጀት ዓመት ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ባንኩ በታሪኩ ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበበት ዓመት መኾኑን ነው። በ2011 በጀት ዓመት ባንኩ ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ 636 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል። እንደ ባንኩ መረጃ ይህ ትርፍ ከ2010 የበጀት ዓመት የ86 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል።
የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠንም በ18 በመቶ አድጐ 14.7 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል። (ኢዛ)