Ethiopian parliament

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ይሾማሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የጤናና የገቢዎች ሚኒስትሮች ይገኙበታል

ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 12, 2020)፦ በተለያዩ የሚኒስትር፣ የሚኒስትር ዴኤታና በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ተሿሚዎች አዳዲስ ሹመት ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ይሾማሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ የጤናና የገቢዎች ሚኒስትሮች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት እንዳስታወቀው ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚያካሒደው መደበኛ ስብሰባ፤ የፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባላት ሹመት በምክር ቤቱ ተመርምሮ ይጸድቃል ብሏል።

ከእነዚህ ሹመቶች ሌላ የሌሎች ሚኒስትሮች ሹመትም ለምክር ቤቱ የሚቀርብና በዚህም ምርመራ ተደርጎ እንደሚጸድቅ ተነግሯል።

የምክር ቤቱ መረጃ ሚኒስትር የሚሾምላቸው መሥሪያ ቤቶች የትኞቹ እንደኾኑ ባይገልጽም፤ በትናንትናው ዕለት የተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የጤና ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፤ እንዲሁም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮችና ኃላፊ ይሾሙላቸዋል።

በዚህም ሹመት በአሁኑ ወቅት የገቢዎች ሚኒስትር በመኾን እያገለገሉ ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኾነው እንደሚሾሙ እየተነገር ነው። ይህ ሹመትም በቅርቡ አምባሳደር ኾነው የተሾሙትን የቀደሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬን ይተካሉ ማለት ነው። የወ/ሮ አዳነች ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መኾን ደግሞ፤ የገቢዎች ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት እንዲመሩ በቅርቡ ከአማራ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነታቸው የለቀቁት አቶ ላቀ አያሌው እንደሚሾሙ ይጠበቃል።

ዶ/ር አሚር አማን ከጤና ሚኒስትርነታቸው በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ ለወራት (አሥር ሳምንት፤ ሁለት ወር ከግማሽ) በቦታቸው ሳይሾምበት የቆየ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ለዚህ ቦታ አሁን በሚኒስትር ዴኤታነት እያገለገሉ ያሉት ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር ኾነው እንዲሠሩ ሹመታቸው እንዲጸድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

ዶ/ር አሚር ከለቀቁ በኋላ ዶ/ር ሊያ የጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን በዋናነት ሲመሩ ቆይተዋል። ባለፈው ሳምንት የካቲት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፤ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው መሰየማቸው አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ