አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣  አቶ ባጫ ጊና፣ ወ/ሮ ያለም ፀጋይ፣ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ፣ አቶ ነብያት ጌታቸው

አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ (በግራ)፣ አቶ ባጫ ጊና (ከላይ መሐል)፣ ወ/ሮ ያለም ፀጋይ (ከላይ በቀኝ)፣ ወ/ሮ ሒሩት ዘመነ (ከታች መሐል)፣ አቶ ነብያት ጌታቸው (ከታች በቀኝ)

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ይገኙበታል

ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 3, 2020)፦ በሚኒስትር ዴኤታነት እያገለገሉ ያሉና በሌሎች በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ 15 ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን ለቀው አምባሳደር ኾነው እንደተሾሙ ተገለጸ። ከእነዚህ ውስጥ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ተካትተዋል።

ዛሬ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ከኾነው መረጃ መሠረት በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከተሾሙት ውስጥ ዘጠኙ በባለሙሉ አምባሳደርነት፣ ስድስቱ ደግሞ በአምባሳደርነት የተሾሙ መኾናቸው ተገልጿል።

አሁን ያሉበትን ሥልጣን ለቀው አምባሳደር ኾነው ይሠራሉ ተብለው በዋናነት የተጠቀሱት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ናቸው። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት የኾኑት አቶ ባጫ ጊና መኾናቸው ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ሒሩት ዘመነም ከሚኒስትርነታቸው ተነስተው አምባሳደር ይኾናሉ።

ሌላዋ ሚኒስትር ወ/ሮ ያለም ፀጋይ እስካሁን የሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት እንደተገለጸው አምባሳደር ኾነው በመሾማቸው ሚኒስትርነታቸውን ይለቃሉ።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጐረቤት አገሮችና የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በየነ መንግሥታት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ይበልጣል አእምሮ አሁን አምባሳደር ከሚኾኑት ውስጥ ተካትተዋል።

ሌላው ካሉበት ተነስተው አምባሳደር በመኾን የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ናቸው።

አቶ ጀማል በከር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፣ በአምባሳደርነት ማዕረግ ተሹመዋል።

አቶ ሽብሩ ማሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፋይናንስና የግዥ ማኔጅመንት ዳይሬክተር ጄኔራል የነበሩ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት አምባሳደር ኾነው ከተሾሙት ስድስቱ የሥራ ኃላፊዎች ውስጥ አንዱ ናቸው።

አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሲሆን፤ ይህም በዛሬው ሹመት ምክንያት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለት ሚኒስትር ዴኤታዎች መነሳታቸውን ያመለክታል።

ዛሬ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና አምባሳደር ኾነው የተሾሙት ባለሥልጣናት የተመደቡበት አገር ባይገለጽም፤ ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ያሳየ ሲሆን፤ በምትካቸውም አዳዲስ ተሿሚዎች ይመደባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በዛሬው ዕለት በባለሙሉ አምባሳደርነትና በአምባሳደርነት ማዕረግ የሾሙዋቸው የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው።

በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት የተሾሙት፤

1. አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣
2. ወይዘሮ ያለም ፀጋይ፣
3. ወይዘሮ ሒሩት ዘመነ፣
4. አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ፣
5. አቶ ባጫ ጊና፣
6. አቶ ይበልጣል አእምሮ፣
7. አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ፣
8. አቶ ነብያት ጌታቸውና
9. አቶ ተፈሪ መለስ ናቸው።

በአምባሳደርነት ማዕረግ የተሾሙት ደግሞ፤

1. አቶ አድጐ አምሳያ፣
2. አቶ ጀማል በከር፣
3. አቶ አብዱ ያሲን፣
4. አቶ ለገሰ ገረመው፣
5. ወይዘሮ እየሩሳሌም አምደማርያምና
6. አቶ ሽብሩ ማሞ መኾናቸው ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ