የቴዲ አፍሮ ክስ የሚታይበት ችሎት ለሁለት ተከፈለ
Ethiopia Zare (ዓርብ መስከረም ፲፮ (16) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 26, 2008)፦ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ክስ እየታየ ያለበት ችሎት ለሁለት ተከፈለ። የዳኞች ድልድል የፊታችን ሰኞ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በመኪና መግጨት ሰው ገድሎ አምልጧል በሚል ክስ ቀርቦበት በክርክር ላይ የሚገኘውና በቃልቲ ማረሚያ ቤት ከታሰረ 5 ወራት ቀን የሞላው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ጉዳዩ የሚቀርብበት ችሎት ለሁለት ተከፍሏል። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፍርድ ቤት ምንጮች እንደገለጹት፣ ችሎቱ እያስተናገደ ያለው የመዝገብ ቁጥር በርካታ በመሆናቸውና የትራፊክ ጉዳይ የሚታይበት ችሎት ስለሆነ በአጭር ጊዜ ለማየት እንዲቻል በሚል ለሁለት እንዲከፈል ተደርጓል።
የመዝገብ ክፍፍል የተደረገውም፣ የመዝገብ ቁጥሮቹ የመጨረሻ ቁጥር ጎዶሎ የሆነ በአንድ ችሎት፣ ሙሉ የሆነ ደግሞ በአንድ ችሎት እንዲደረግ መመሪያ ተላልፏል። ችሎቶቹም አሁን ያለው 8ኛ ወንጀል ችሎት እና 15ኛ ወንጀል ችሎት ተብለዋል።
ጉዳዩን እየተመለከቱ የነበሩት የስምንተኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ልዑል ገብረማርያም ሲሆኑ፣ እንደ ምንጮቻችን ከሆነ ለሁለት ከተከፈሉት ችሎቶች የትኛውን እንደሚያስችሉ ከፊታችን ሰኞ በፊት አይታወቅም።
የዳታ ክፍል ሠራተኞች እየሠሩ ባለው መረጃ መሠረት፣ ሙሉ ቁጥር የያዙ መዝገቦች ዳኛ ልዑል ያስችሉት በነበረው 8ኛ ወንጀል ችሎት ሲመደቡ፣ ጎዶሎ ቁጥር ያላቸውን ደግሞ 15ኛ ወንጀል ችሎት እያዛወሯቸው ነው።
የአርቲስት ቴዲ አፍሮ የክስ መዝገብ ቁጥር 62266 በመሆኑና የመጨረሻው ቁጥር ሙሉ በመሆኑ፣ መዝገቡ እዚያው ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ሳይመደብ እንደማይቀር ምንጮች ግምታቸውን ገልጸዋል።
ቴዲ አፍሮ የቀረበበት ክስና ዓቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ማስረጃ እንዲከላከል በመበየኑ፣ በቀጣዩ መስከረም 28 ቀጠሮ የመከላከያ ማስረጃውን ይዞ ይቀርባል በሚል የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዕለቱ አንድ ተጨማሪ ጠበቃ እንደሚቆምለት ለማወቅ ተችሏል።
ፍርድ ቤት ከመዘጋቱ በፊት ባለው የቴዲ አፍሮ የመጨረሻ ቀጠሮ የተሰጠውን ብይን በማስመልከት፣ ጠበቃው በሰጡት መግለጫ ምክንያት የ50 ቀናት እስር ተፈርዶባቸው ጉዳያቸው በይግባኝ ያለ መሆኑ አይዘነጋም።
የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ በተደረገው 7ኛው የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ መገኘታቸውን ጠቅሰን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በቀጣዩ ቀጠሮ ተጨማሪ ጠበቃ ተደርቦ ለአርቲስቱ ይከራከርለታል ተብሎ ይጠበቃል።



