Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፲፯ /17 ቀን ፳፻፩/2001 ዓ.ም. September 27, 2008)፦ ኢትዮጵያን በመጥፎም ሆነ በበጐ ጐን ከዓለም አስር ሀገራት ተርታ የሚያሰልፏት ሩሴል አቮ የተባሉ ደራሲ (Top 10 of everything 2009) በሚል መጽሐፋቸው ያሰፈሯቸው ጉዳዮች አንዳንዶቹ የሚታወቁ ሌሎቹ ደግሞ ፈጽሞ የማይታወቁ አስገራሚ ነገሮች ናቸው። ለምሣሌ የዓለማችን ዋነኛ ሞቃት ሥፍራ ዳሎል በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ 94.3 ዲግሪ ፋራናይት ወይም 34.6 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት እንዳለው በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል፤ ከዳሎል ቀጥሎ በሞቃታማነቱ የተጠቀሰው በኤርትራ የሚገኘው አሰብ ነው።

 

ሌላም አስገራሚ መረጃ በመጽሐፉ ላይ ሠፍሯል፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋ በርካታ ሰዎች ከሞቱባቸው ሀገራት በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፤ ይህ ደረጃ እ.ኤ.አ. ከ1900-2007 የተመዘገቡ የተፈጥሮ አደጋ የሞት መጠኖችን መሠረት በማድረግ የተገኘ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ 415 ሺ 837 ሰዎች በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በወረርሽኝ፣ በከፍተኛ ሙቀት፣ በጎርፍና በመሳሰሉት መሞታቸውን መጽሐፉ የቤልጂየምን ሉቪያን ዩኒቨርሲቲ ዋቢ አድርጓል። በዚህ ምድብ ቻይና በአንደኛነት፣ ሕንድ በሁለተኛነት፣ ሶቭየት ህብረት በሦስተኛነትና ባንግላዴሽ በአራተኛነት ሠፍረዋል።

 

እ.ኤ.አ. በ1868 ዓ.ም. እንግሊዞች ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋር ባደረጉት ጦርነት ወቅት፣ በእንግሊዛዊው ሻለቃ ባሬት ሊኦናርድ ወደ ሀገራችን እንደገባች በሚነገርላት የአቢሲኒያ የድመት ዝርያ ኢትዮጵያ ከዓለም በስድስተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ አድርጓታል።

 

የቶፕ ቴን መነጽሩ ኢትዮጵያን በ38 ሚሊዮን 102 ሺህ 688 የቀንድ ከብቶች ከዓለም 7ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት፣ ጐረቤት ሀገር ሱዳንን በ38 ሚሊዮን 325 ሺህ የቀንድ ከብቶች 6ኛ መሆኗን አስታውቋል። ይህ ማለት ደግሞ ሱዳንን ከአፍሪካ አንደኛ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ሁለተኛ ያደርጋታል።

 

ዝቅተኛ የስብ ይዘት ያላቸው ምግቦች የሚመገቡ በርካታ ሰዎች ካሉባቸው ሀገራት ተርታ ኢትዮጵያ በ3ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ በቀን የአንድ ሰው የስብ ፍጆታ በአማካይ 21 ግራም መሆኑ ተገልጿል። በካሎሪ አወሳሰድ በኩልም ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ካሎሪ ከሚመገቡ ሀገራት ተርታ በቀን በአማካይ 1850 ካሎሪ በመውሰድ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ስትሰፍር በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኤርትራ የካሎሪ ፍጆታዋ በቀን በአማካይ 1500 ካሎሪ ነው።

 

ኢትዮጵያ በዓመት ከ1000 ሰዎች መካከል 10 ነጥብ 2 በመቶው ጋብቻ የሚፈጸባት ሆና በከፍተኛ የጋብቻ መጠን ከአስር ሀገራት ሦስተኛ ሆናለች። በአንደኛ ደረጃ የነበረችው በርባዶስ፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ቬትናም መሆኗ ታወቋል።

 

የከተሞች አለመስፋፋት በስፋት ከሚታዩባቸው አስር ሀገራት መካከል ቡሩንዲ በአንደኝነት ስትቀመጥ እ.ኤ.አ. እስከ 2005 ድረስ ኢትዮጵያ 16 በመቶ ህዝቧ ብቻ በከተማ በመኖሩ ዝቅተኛ የከተሞች መስፋፋት ከሚታይባቸው ሀገራት በ8ኛ ደረጃ ሠፍራለች።

 

አይ.ኤም.ኤፍ. እንደገለፀው በኢትዮጵያ በ2007 የተመዘገበው የግሽበት መጠን 17.8 በመቶ ደርሷል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የግሽበት መጠን በማስመዝገብ ከአስር ሀገራት 7ኛ ሆናለች። በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠችው ዚምባቡዌ የ16,170 በመቶ ግሽበት አስመዝግባለች።

 

በድህነት ረገድም ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያና ጊኒ ቢሳውን በመከተል ከድሃ ሀገራት ተርታ 5ኛ ሆናለች።

 

ኢትዮጵያን በቶፕ ቴን ዝርዝር ውስጥ እንድትሠፍር ካደረጓት መመዘኛዎች መሐከል ወደብ አልባ መሆኗም ይጠቀሳል። በቆዳ ሽፋናቸው ስፋትና በወደብ አልባነታቸው ከሚጠቀሱት አስር ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን መጽሐፉ አስፍሯል። ይሁን እንጂ በከተማ ጽዳት፣ በመኪና አደጋ በሚደርስ ሞትና በሌሎች በአስከፊነታቸው በሚጠቀሱ ጉዳዮች ላይ መጽሐፉ በግልጽ ያሠፈረው መረጃ የለም።

 

ኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች የመኪና ባለቤት ያልሆኑባት ሀገር በመባልም በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እ.ኤ.አ. እስከ 2005 ድረስ በኢትዮጵያ 73,500 መኪኖች ሲኖሩ፣ ይህም ለሰው ሲካፈል አንድ መኪና ለ993.9 ሰዎች እንደሚደርስ መረጃው ያመለክታል።

 

በግለሰብ ደረጃ ደግሞ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) በሚያዘጋጀው የዓለም ሻምፒዮና እስከ ጃፓን ኦሳካው ሻምፒዮና ድረስ በርከት ያሉ ሜዳሊያዎችን በመውሰድ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

 

በመጽሐፉ ላይ የሠፈሩት የኢትዮጵያ ቶፕ ቴን መገለጫዎች አብዛኛዎቹ የድህነት ገጽታ ያላቸውና በቀጥታም ከድህነት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። በማኅበራዊ ጉዳዮች መጥፎ ጐኖች አለመነሳቱንና የተፈጥሮ አደጋም ቢሆን ከድርቅ በቀር የጥፋት በትሩን በብዛት እንዳላሣረፈባት የሚስተዋል ሲሆን፣ ከወደብ አልባነቱ ጋር የተያያዘው ጉዳይ የፖለቲካ ውጤት መሆኑ ይታወቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ