የሕወሓት መግለጫና የምርጫ ቦርድ ምላሽ
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (በግራ)፣ የሕወሓት ዓርማ (መሐል)፣ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል (በቀኝ)
ሕወሓት በክልሉ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል
እንዲህ ያለው ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ አለመኾኑን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አሳወቁ
"ሕገወጥ የሰፈር ምርጫ አይካሔድም” አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 5, 2020)፦ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት በክልል ደረጃ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንና ለዚህም የፖለቲካ ድርጅቶች ይተባበሩት ዘንድ ጥሪ ያስተላለፈበት መግለጫ፤ የፖለቲካውን ትኩሳት ሙቀት ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ይህ ፈጽሞ ሕገ መንግሥታዊ ያለመኾኑን አስታውቋል።
ሕወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫው ውሳኔ ያሳለፈባቸውን ጉዳዮች ካብራራ በኋላ፤ ውሳኔ ላይ ደርሸበታለሁ ካላቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ፤ የምርጫ መራዘምና ሕገ መንግሥቱን ለማስተርጐም የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል ከኾነ ክልላዊ ምርጫን በክልል ደረጃ ለማካሔድ ዝግጅት እንዲደረግ መወሰኑን የሚጠቁም ነው። የሕወሓትን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!
“ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው ብልጽግና ከመስከረም 25 በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም እድል የማይኖር በመኾኑ፤ የአገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት እድል መፈጠሩ የማይቀር ይኾናል” በማለትም መግለጫው አመልክቷል። ሕወሓት እንደዚሁ ዐይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ አገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ እንደነበረም ይጠቅሳል።
የትግራይ ሕዝብ በመሥዋዕትነቱ በተከለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት እንደማይፈቅድም ገልጿል። ለዚህም ሲባል ከትግራይ ሕዝብና ለትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመኾን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የሕዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ስለመወሰኑ በዚሁ መግለጫው ላይ አስታውቋል።
ይህም እንቅስቃሴ የፀረ ኮሮና ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈጸም እንደኾነም መግለጫው ያትታል። አያይዞም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ሕልውናቸው ያረጋገጠውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሐይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ ከዚህ አጋጣሚ የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል ብሏል።
የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተወያይቶ ውሳኔ የደረሰበት ነው ብሎ የጠቆመው መግለጫው የብልጽግና ፓርቲ፤ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም የጠየቀበት ነው። ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልጽ መስፈርት መሠረት አሻሚ ኹኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ፤ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን እንደማይቻልም ገልጿል። በመኾኑም ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፊያ በአስቸኳይ እንዲቆም በመግለጫው የጠየቀው ሕወሓት፤ አሁንም የኮሮናን ወረርሽኝ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ኾነ አገራዊ ምርጫን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማዕቀፍ ውስጥ በመኾን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች ተሳታፊ መኾን አለባቸው ብሏል። ይህንንም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ አገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻችም ጠይቋል።
እንዲህ ያለው ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ አለመኾኑን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አሳወቁ
እንዲህ ያለውን ይዘት የያዘውን የሕወሓት መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ለኢቢሲ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የትኛውንም ምርጫ የማካሔድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መርጫ ቦርድ ብቻ እንደኾነ አስታውቀዋል። የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ መግለጫ እንዳወጣና መግለጫውን ስለመመልከታቸው የገለጹት ወ/ት ብርቱካን፤ በመግለጫው እንደተገለጸው ግን ክልላዊ ምርጫ እንዲደረግ ቁርጥ ያለ ውሳኔ ስለመወሰናቸው እርግጠኛ ያለመኾናቸውን ገልጸዋል። ይህንንም ከመግለጫው በትክክል ማየት የማይቻልና ምናልባት ዝግጅት የሚል ቃል የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚዎች መጠቀማቸውን ግን ጠቅሰዋል። “በሌላ በኩል ለእኛ ፎርማሊ የደረሰን ነገር የለም። በክልሉ ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ውሳኔ መደረጉን ፓርቲውም ኾነ የክልል አስተዳደሩ ያሳወቀን ነገር የለም” በማለት አብራርተዋል።
“ያም ኾነ ይህ ግን፤ በዚያ ሁኔታ በክልል ደረጃ የሚደረግ ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማስፈጸም አስበውም ወስነውም ከኾነ፤ ትክክለኛ አካሔድ አይደለም” በማለት አስታውቀዋል። ትክክለኛ ካለመኾኑም በላይ ደግሞ ሕገመንግሥታዊ አይኾንም፤ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 102 ላይ አንድ የምርጫ ቦርድ ብቻ ያለመኾኑን አመላክተዋል።
“ይህ የምርጫ ቦርድ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ) አገራዊ ነው። በክልል የሚመራው ቦርድ በፌዴራልም ኾነ በክልል ደረጃም ቢኾን፣ በቀበሌም፣ በጐጥም የሚደረጉ ምርጫዎች ካሉ ተጠብቆ በገለልተኝነቱ ምርጫውን የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው ለዚህ ቦርድ ነው” ብለዋል።
ስለዚህ የትግራይ ክልልም ኾነ ክልሉ የሚመራው ፓርቲ ወይም ሌላ ክልል፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ ተነስቶ፤ የምርጫ ሰሌዳን፣ የምርጫ አፈፃፀምንና የምርጫ ዝግጅትን በተመለከተ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ወይም ደግሞ ለመፈጸም እቅድ ቢያወጣ፤ ከሕገ መንግሥት ውጭ ነው የሚኾነው በማለት፤ የትኛውም በአገሪቱ የሚካሔድ ምርጫ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ አማካኝነት የሚካሔድ መኾኑን አስረድተዋል።
በምርጫ ቦርድ በኩል ምርጫ ለማካሔድ ሙሉ ዝንጅት ተደርጎ፤ እንቅስቃሴ ተጀምሮ፤ ምርጫ ሰሌዳውም ማውጣቱ የሚታወቅ ስለመኾኑ ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፤ “ይህ አጠቃላይ ምርጫ የፓርላማንና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን የሚያካትት ነው። በሕገ መንግሥቱ ላይ እነዚህን ምርጫዎች ማደራጀትና ማካሔድ የእኛ ሥልጣን ነው” በማለት የትግራይ ክልል ወሰደ የተባለውን እርምጃ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ እንደሌለው አስታውቀዋል።
የፓርላማውንም ኾነ የክልል ምክር ቤት ምርጫዎች የማስተናገድና የማካሔድ ሥልጣን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መኾኑንም በማከል፤ እነዚህ ሁለት ምርጫዎች አንድ ላይ የሚካሔዱ መኾኑንም አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በተለየ ሁኔታ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በተለየ ጊዜ ምርጫ ሊደረግ ይችላል። ይህንኑም የተለየ ምርጫን የሚያስፈጽመው ምርጫ ቦርድ ነው። ሥልጣኑ የቦርዱ ነው። ምናልባት የትግራይ ክልል በተለየ ጊዜ ተለይቶ እኛ ጋር ምርጫ ሊደረግ ይችላል የሚል ከኾነ፤ ለኢትየጵያ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረብ የሚችል መኾኑንም ሳይገልጹ አላለፉም።
“ከቦርዱ እውቅና ውጭ ምርጫውን አደርጋለሁ ብሎ ከቀጠለስ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ት ብርቱካን የሰጡት መልስ፤ “ምርጫ ማከናወንም፣ ውጤት መግለጽም፣ በእያንዳንዱ ሥልጣን ርክክብ ላይ ኃላፊነቱን የሚወስደውን ፓርቲ ተወዳዳሪን ሕጋዊነት ማረጋገጥ የቦርዱ ኃላፊነት ኾኖ ሳለ፤ ሌላ አካል ቢያደርገው በፍጹም ሕጋዊነት ሌላው ነገር ነው። ግን ይህ ከእኛ ኃላፊነት ውጭ ነው የሚኾነው። ግን ተስፋ የማደርገው ክልሉ በዚያ መስመር አይሔድም የሚል እምነት አለኝ” የሚል ነው።
"ሕገወጥ የሰፈር ምርጫ አይካሔድም” አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል (የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ)
የሕወሓት መግለጫ ከወጣ በኋላ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል ባሰፈሩት አጭር መልእክት፤ “በዜጎች ክብር መሥዋዕትነት የቆሙ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የሚጥስ ሕገወጥ የሰፈር ምርጫ አይካሔድም” ብለዋል። አያይዘውም ማንኛውም መሰል ፍላጎትና ሙከራም ካለ በግንባር ቀደምትነት ለሕገ መንግሥቱ ዘብ በቆመ ኃይል፤ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያዊ የተባበረ ሕዝባዊ ትግል ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶበት ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ይደረጋልም ብለዋል። (ኢዛ)



