Best Western Plus Addis Ababa

በአዲስ አበባ ከሚገኙት ባለኮኮብ ሆቴሎች አንዱ የኾነው ቤስት ዌስተርን ፕላስ (ፎቶ ከቡኪንግ ዶት ኮም፤ ፎቶው ከዜናው ጋር በቀጥታ ተያያዥ አይደለም)

ብሔራዊ ባንክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰጥ ብድር አመቻቸ

ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 14, 2020)፦ በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች የኮሮና ወረርሽኝ በአገሪቱ መከሰቱ መገለጽ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በየወሩ ከ35 ሚሊዮን ዶላር በላይ (1.57 ቢሊዮን ብር) ገቢ እያጡ መኾኑን የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማኅበር ገለጸ።

በአሁኑ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሆቴሎች ማኅበር ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን እንዳስታወቀው ደግሞ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ በለኮኮብ ሆቴሎች ብቻ በወር በአማካይ 35 ሚሊዮን ዶላር እያጡ መኾኑን በ126 ሆቴሎች ላይ የተደረገ ጥናት አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ድርጅቶች በወቅቱ የደረሰባቸውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተበዳሪዎች የሥራ ማስኬጃ የሚኾን ብድር እንዲመቻችላቸው ወስኗል። በዚህም መሠረት ባንኮች ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተበዳሪዎቻቸው የሚኾን ገንዘብ ከብሔራዊ ባንክ በአምስት በመቶ ወለድ ተበድረው፤ ለተበዳሪ ደንበኞቻቸው በአምስት በመቶ ወለድ እንዲያበድሩ አሳውቋቸዋል።

ይህም ጉዳታቸውን ለመቀነስ ያግዛል የተባለ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮቹ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሠጡት ብድር ልክ የተሰላ ገንዘብ መድቦላቸዋል። ከሁሉም ባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ የተመደበለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፤ 850 ሚሊዮን ብር ያገኛል ተብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ