ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት፣ አቶ ሸዋንግዛው ገብረሥላሴ

ኢንጂንየር ይልቃል ጌትነት የኢአን ሊቀመንበር (በግራ) አቶ ሸዋንግዛው ገብረሥላሴ የመአሕድ ፕሬዝዳንት (በቀኝ)

የ76 ፓርቲዎችንም ጉዳይ እየመረመረ ነው

ኢዛ (ዓርብ ግንቦት ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 15, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ የፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ የተደረገላቸውን ጥሪ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አላሟሉም ያላቸውን 27 የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታወቀ።

ቦርዱ ዛሬ ዓርብ ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ፓርቲዎቹ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞው ሰርቲፊኬት የነበራቸውና በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡ በደብዳቤ ያሳወቃቸው ቢሆንም፤ ይህንን ባለማድረጋቸው እርምጃው መወሰዱን የሚያመለክት ነው።

በቀድሞ ሕግ ሰርቲፊኬት የነበራቸውና በቀድሞ ሕግ ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ሕግ መሰርቱን እንዲያሟሉ ማሳወቁን የሚገልጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ106ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76ቱ ሰነዶቹን ያቀረቡ ሲሆን፤ በሕግ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመኾኑ እየተመረመረ መኾኑን ገልጿል።

ይህ የቦርዱ መረጃ ከ76ቱ ውስጥ በትክክል መስፈርቱን አሟልተዋል ወይስ አላሟሉም የሚለውን በመመርመር ተጨማሪ እርምጃ የሚወስድ ስለመኾኑ ያሳያል።

የዛሬው የቦርዱ መረጃ ከሰረዛቸው ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢአን)፣ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ)፣ የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ትወብዴድ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ)፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) ይገኙበታል። የምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መረጃ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞ ሕግ ሰርተፍኬት የነበራቸው እና በቀድሞው ሕግ ምዝገባ ጀምረው ለነበሩ 106 ፓርቲዎች በአዲሱ ሕግ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ በደብዳቤ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ከቦርዱ ደብዳቤ ከደረሳቸው 106 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶችን ያቀረቡ ሲሆን በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ ስለመሆኑ እየተመረመረ ይገኛል፡፡

ምርመራውም፤

• ፓርቲዎቹ በደብዳቤ የተገለጸላቸውን ነጥቦች ሁሉንም ማሟላታቸውን ማረጋገጥ (የሕገ ደንብ ለውጥ ጠቅላላ ጉባዔ ሰነዶች አቀራረብ፣ የመስራቶች ፊርማ … የመሳሰሉት)
• የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ማሟላት የሚገባቸውን የመሥራች አባላት ብዛት ትክክለኛነትን ለመፈተሽ ካቀረቡት የመሥራች አባላት ዝርዝር ናሙና የማውጣት
• ናሙናዎቹ በትክክል ግለሰቦቹ የተፈረሙ መሆናቸውን ወደተፈረሙበት ቦታ በመላክ ማረጋገጥ
• የሕገ ደንብ ለውጦችና፣ የጠቅላላ ጉባዔ ሰነዶች በትክክል መያያዛቸውን ማረጋገጥን ያጠቃልላል፡፡

ይህ እንደተጠናቀቀም ሰነዶቻቸው ካስገቡት 76 ፓርቲዎች መካከል ምን ያህሎቹ መስፈርት እንዳሟሉ በቦርዱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡

ነገር ግን የሚጠበቅባቸውን ሰነድ ማስገባት ያልቻሉ እና ጊዜ እንዲራዘምላቸው የጠየቁ 15 የፓለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ከነዚህ ፓርቲዎች መካከል ከስር የተጠቀሱት የ13ቱ አጥጋቢ ምክንያት ባለማቅረባቸው እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል፡፡

የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ሳያገኙ የተሰረዙ ፓርቲዎች ዝርዝር የሚከተለው ነው

1. የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሔደ
2. የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
3. የየም ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የብዴን) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሔደ
4. የደንጣ ዱባሞ ክችንችላ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - የመሥራች አባላት ዝርዝርም ያላቀረበ፣ ጉባዔ ያላካሔደ
5. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ (ኮንግረስ) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
6. የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ትወብዴድ) - ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሔደ
7. የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ፣ ጉባዔም ያላካሔደ
8. የኢትዮጵያን አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኢአዴድ) - ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሔደ
9. የመላው አማራ ሕዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
10. የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢአን) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
11. የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ደቡብ ኮንግረስ) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ
12. የሸኮና አካባቢው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሸአሕዲድ) -ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሔደ
13. ነፃነትና ሰላም ለኢትዮጵያ ህብረት ፓርቲ (ነፃነትና ሰላም) - የመሥራች አባላት ዝርዝር ያላቀረበ

በሌላ በኩል ሌሎች 14 ፓርቲዎች ደግሞ ከቦርዱ በተደረገው ጥሪ መሰረት ሰነዶቻቸውን ከነአካቴው ያላቀረቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መዋሃዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የነዚህ 14 ፓርቲዎች እንዲሰረዙ ቦርዱ ወስኗል፡፡

በመሆኑም ሰነድ ባለማምጣታቸው እንዲሰረዙ የተሰወኑት ፓርቲዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1. የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ
2. መላው ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
3. የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ
4. የሐድያ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
5. የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት
6. የዲል ወቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ
7. የቤንች ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት
8. የስልጤ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
9. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
10. የሱማሌ አንድነት ፓርቲ
11. ነፃነት ለአንድነትና ለፍትሕ ፓርቲ
12. ብሔራዊ ተሀድሶ ለሰላም ልማት
13. የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ህብረት
14. የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ

ሁለት ፓርቲዎች ሰነዶችን ማቅረብ አለመቻላቸው በፓርቲው የውስጥ ችግር የተነሳ መሆኑ ስለታመነበት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን የኮቪድ ወረርሽን በሚያበቃበት ወቅት አንዲያከናውኑ ቦርዱ ሲወስን ሌሎች ሰነዶቻቸው ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ እየተገመገሙ ይገኛል፡፡

በልዩ ሁኔታ የሰነድ ካስገቡ ፓርቲዎች ጋር ሰነዶች እንዲታይላቸው የተደረጉ ፓርቲዎች

1. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)
2. ወለኔ ሕዝቦች ፓርቲ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ