Teddy Afroአዲሱ የቴዲ ጠበቃ የዳኛው ረዳት ነበሩ

ቴዲ የፊታችን ኀሙስ መከላከያ ይዞ ይቀርባል

Ethiopia Zare (ዓርብ መስከረም ፳፫-23 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 3, 2008)፦ የዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮን) የክስ ሂደት ሲዳኙ የነበሩት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም "ለጊዜው" ከችሎት የተነሱ ሲሆን በምትካቸው ዳኛ መሐመድ ዑመር ተተክተዋል። በተያያዘ ለቴዲ አፍሮ አዲስ የተቀጠሩለት ሁለተኛው ጠበቃ የአቶ ልዑል ረዳት ዳኛ ሆነው ሠርተዋል።

 

ከታሠረ አምስት ወራትን ያስቆጠረው ቴዲ አፍሮ፣ ከፍርድ ቤቱ የዕረፍት ጊዜ በኋላ የፊታችን ኀሙስ ባለው የመጀመሪያ ቀጠሮ፣ የመከላከያ ማስረጃዎቹን ይዞ ሲቀርብ አዲስ ዳኛ እንደሚጠብቀው ታውቋል።

 

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን እንደገለጹት፣ ችሎቱ እያስተናገደ ካለው መዝገብ ብዛትና፣ የሚቀርቡትን የትራፊክ ክሶች በአጭር ጊዜ ለማየት በሚል፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት የነበሩ 679 መዝገቦች በጎደሎና በሙሉ ቁጥር ተለይተው፣ ሙሉ ቁጠሮቹ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፣ ጎደሎ ቁጥሮች ደግሞ 15ኛ ወንጀል ችሎት በሚል ለሁለት እንዲከፈሉ ተደርጓል።

 

የቴዲ አፍሮ የክስ መዝገብ ቁጥር 62266 በመሆኑና የመጨረሻው ቁጥር ሙሉ ስለሆነ 8ኛ ወንጀል ችሎት የደረሰው ሲሆን፣ ይህን ችሎት ያስችሉ በነበሩት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ምትክ፣ ዳኛ መሐመድ ዑመር በጊዜያዊነት እንዲሠሩ በደብዳቤ ተመድበዋል።

 

ከዚህ ችሎት ለሁለት የተከፈለውንና ጎደሎ የሆኑ የመዝገብ ቁጥሮች የያዘውን 15ኛ ወንጀል ችሎት ደግሞ ጌታቸው ይርጋ የተባሉ ዳኛ እንዲያስችሉት መመደባቸው ታውቋል።

 

በሌላ በኩል ከቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ጋር በጋራ ሆነው እንዲከራከሩ የተቀጠሩት አቶ አምሃ በድሉ የተባሉ አዲስ ጠበቃ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ በዲግሪ ከተመረቁ በኋላ፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎቶች ለሦስት ዓመት በረዳት ዳኝነት አገልግለዋል።

 

ከፍርድ ቤት ከለቀቀቁ ጀምሮ ለአራት ዓመት በጥብቅና ሞያ ላይ በማገልገል ላይ ናቸው። ቴዲ አፍሮ የፊታችን ሐሙስ በሚኖረው ቀጠሮ አቶ አመሃ ከቀድሞው ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ ጋር ሆነው ይቀርቡለታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ