Ambassador Dina Mufti

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አምባሳደሩ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዙምባብዌ፣ ስዊድን፣ ኬንያና ግብጽ አገልግለዋል

ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 9, 2020)፦ ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩትና በኬንያ እና በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመኾን ሲሠሩ የቆዩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ እንደገና ቃል አቀባይ ኾነው ተሾሙ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዘም ላሉ ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ በይበልጥ ይታወቁበት የነበረው ከለውጡ በፊት በቃል አቀባይነታቸው ነበር። ከለውጡ በኋላ ግን መጀመሪያ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር፤ ቀጥሎም በግብጽ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ በኾነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መረጃ፤ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተመልሰው የቀድሞውን ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል። ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ነብያት ጌታቸው፤ በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ኾነው ባለፈው መጋቢት መሾማቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

እንደኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮ መረጃ፤ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በቀደሙት ዓመታት በአሜካና በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በአማካሪነት ሲያገለግሉ ነበር። ከዚያም በኋላ በዙምባቡዌ ዋና ከተማ ሐራሬ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ ሲሆን፤ በመቀጠልም በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው አገልግለዋል። ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኾነው ሲያገልግሉ ከቆዩ በኋላ ነበር ወደ በኬንያ በአምባሳደርነት ተሹመው የሔዱት። ከኬንያ በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች፤ አምባሳደሩ ከግብጽ መልስ በአዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ውስጥ ለጥቂት ወራት በቢሮ ውስጥ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ነው፤ በድጋሚ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኾነው የተሾሙ መኾናቸውን አስረድተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!