ግብጽ አዲሱ ድርድር ላይ እንቅፋት እየኾነች ነው
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የግብጽን አቋም ስስታም ብለውታል
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 17, 2020)፦ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ለተከታታይ ቀናት ሲካሔድ የቆየው ድርድር አሁንም በግብጽ ግትር አቋም በድጋሚ የተጀመረው ድርድር ላይ እንቅፋት ስለመኾኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ አድርጓል።
አምስት ቀናትን የያዘው የሦስቱ አገራት ሰሞናዊ ድርድርን በተመለከተ፤ በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹት፤ ግብጽ የዓባይን ውኃ ብቻዬን ልጠቀም የሚለው ግትር አቋሟ እንደ አዲስ ለተጀመረው ድርድር እንቅፋት ኾኗል።
ግብጽ አንድ እግሯን ድርድሩ ላይ፣ አንድ እግሯን ደግሞ የጸጥታው ምክር ቤት አስቀምጣ መደራደርን መምረጧን በመጥቀስ፤ “ድርድሩ ግብጻውያኑ የፈለጉትና የጠየቁት ሁሉ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፤ የሚሰጡት ግን የላቸውም” በማለት የግብጽን ወቅታዊ አቋም በመኮነን ተናግረዋል።
በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር ያለውን ሁኔታ በተመለከተ አቶ ገዱ ጠንከር ያለ መግለጫ በሰጡበት መድረክ፤ የግብጽ አቁምን፤ “ከካይሮ የሚታየው የበዛ ስስት ድርድሩ ላይ እንቅፋት ኾኗል” በማለት ጭምር እየተካሔደ ያለው ሰሞናዊ ድርድር በግብጽ እየታወከ ስለመኾኑ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት የጋራ ተጠቃሚነት ቢኾንም፤ የግብጽ ባለሥልጣናት ፍላጎት ደግሞ ከዚህ በተለየ ስለመኾኑ የሚያመለክተው የአቶ ገዱ መግለጫ፤ “የግብጽ መሪዎች የኢትዮጵያ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ መቆየት እንዴት ያስደስታቸዋል?” በሚልም ጥያቄ አዘል መልእክት አክለዋል።
ግብጽ ከመርኅ ስምምነቱ ባለመውጣትና የሦስትዮሽ ድርድሩን በመቀጠል ፍትሐዊና ምክንያታዊ የዓባይ ወኃ አጠቃቀም የሚያረጋግጥ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለበትም በአጽእኖት ጠይቀዋል። የግብጽ አካሔድ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነውና፤ ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ይህንን እንዲገነዘብም ጥሪ አስተላልፈዋል።
አቶ ገዱ በዚህ መግለጫቸው ግብጽ ልትገነዘብ የሚገባውና መፍትሔ የሚኾነው ብለው የተናገሩት፤ “ኢትዮጵያ አሁንም የዓባይ ባለቤትም፤ ዋነኛዋ የመፍትሔው ወሳኝ አገር እንደመኾንዋ፤ ግብጽ ሁሌም ላለመስማማት ራሷን ያዘጋጀች ቢኾንም፤ መፍትሔው ውይይትና ድርድር ነው” የሚል ነው። (ኢዛ)



