የኦነግ አመራሮች

የኦነግ አመራሮች በሒልተን ሆቴል መግለጫውን በሰጡበት ወቅት

ከሕወሓት ጋር ግንኙነት የለኝም አለ፣ የታሰሩ አባሎቼ ይፈቱልኝም ብሏል
አቶ ዳውዲ ኢብሳ መግለጫው ከእኔ እውቅና ውጭ ነው አለ

ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 10, 2020)፦ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ታስረውብኛል ያላቸውን አመራሮችና ደጋፊዎቹ እንዲፈቱለት ሲጠይቅ፤ ከሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም ብሏል። በመግለጫው አቶ ዳውድ ኢብሳ ያልተገኙ ሲሆን፤ ስለመግለጫው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዛሬ ሰኞ ነኀሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በፓርቲውና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ፤ ተዘግተውብኛል ያላቸውን ጽሕፈት ቤቶቹ እንደከፈቱለትም ጠይቋል።

ኦነግ የአገሪቱን እና የፓርቲውን ሕግ በማክበር ድርጅቱን በማደስ የበለጠ እየሠራ መኾኑን የሚያመለክተው መግለጫው፤ ኦነግ ከሕወሓት ጋር ይሠራል በሚል የሚቀርብበትን ክስ “መሠረተ ቢስ” ነው ብሏል።

ከሕወሓት ጋር የመጠራጠርና የሥጋት እንጂ የትብብርም ኾነ አብሮ የመሥራት ታሪክ የለኝም ብሏል።

ከኦነግ ሸኔ ጋርም በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ መዋቅር ከእውቅናው ውጭ መኾኑንና፤ ነገር ግን በዚህ ቡድን ተጠርጥረው ከ600 በላይ የሚኾኑ ደጋፊዎቼ ታስረውብኛል ብሏል።

በቅርቡ አቶ ዳውድ ኢብሳን ያላሳተፈው ስብስብን በተመለከተም በአስቸኳይ ስብሰባው እውቅና በመነፈጋቸው በአመራሩ መሐል ያለው ክፍተት በፓርቲው የሕግ ኮሚቴ እየታየ ያለ ጉዳይ ስለመኾኑም በዚሁ መግለጫ ላይ ተገልጿል።

በዛሬው መግለጫው ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ ያልተገኙበት ነው። ኦነግ የዛሬውን መግለጫ በሒልተን ሆቴል የሰጡት የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሳ ቢቂላ እና ፓርቲውን በቃል አቀባይነት የሚያገለግሉት አቶ ቀጄላ መርዳሳና አቶ ቶሌራ አደባ ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ