አዲሷ ከንቲባ አዲስ አበባን የሚመጥን የጸጥታ መዋቅር እንደሚገነቡ አስታወቁ
አዲሷ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
የጸጥታ ምክር ቤት ለማቋቋም መክረዋል
ኢዛ (ማክሰኞ ነኀሴ ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 25, 2020)፦ አዲሷ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ ከተማን የሚመጥን የጸጥታ መዋቅር እንደሚገነቡ አስታወቁ።
ከሹመታቸው ቀን ጀምሮ በተለያዩ ሥራዎች የተወጠሩት አዲሷ ምክትል ከንቲባ፤ ዛሬ ማክሰኞ ነኀሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጸጥታ ዘርፍ አካላትና ከክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ለከተማዋ የሚመጥን የጸጥታ መዋቅር ይገነባል ብለዋል።
የሰላም እሴቶችን በማበልጽግ፤ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመከላከል፤ እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ነዋሪውን ያሳተፈ የጸጥታ ምክር ቤት ማቋቋም በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክክር ስለመደረጉም የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሲክሬታሪያት ጽ/ቤት አስታውቋል።
አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመኾኑ መጠን፤ የነዋሪዎቿን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ የከተማ መስተዳድሩ ቀዳሚው ሥራ እንደሚኾን ምክትል ከንቲባዋ መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)



