ቴዲ አፍሮ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባል
ላለፉት 176 ቀናት በእስር ቆይቷል
Ethiopia Zare (ኀሙስ መስከረም ፳፱-29 ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 9, 2008)፦ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. ለመጨረሻ ጊዜ ቀርቦ የነበረው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ከ75 ቀናት በኋላ ዛሬ (ኀሙስ መስከረም 29) ለመጀመሪያ ጊዜ በያዝነው አዲስ ዓመት ፍርድ ቤት ይቀርባል። ቴዲ አፍሮ ላለፉት አምስት ወራት ከ26 ቀናት በድምሩ 176 ቀናት በእስር ላይ ቆይቷል።
በዛሬው ዕለት ቴዲ አፍሮ በተከሰሰበት ክስ የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት መቀጠሩን መዘገባችን አይዘነጋም። በዚሁ መሠረት ችሎቱ ዛሬ የመከላከያ ማስረጃውን ይሰማል ተብሎ ይጠበቃል።
የቴዲን ጉዳይ የሚያየው ችሎት ዳኛ የነበሩት ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ተነስተው በምትካቸው በጊዜያዊነት የተመደቡት ዳኛ መሐመድ ዑመር ችሎቱን የሚያስችሉ ሲሆን፣ ከቴዲ አፍሮ ጠበቃ ሚሊዮን አሰፋ በተጨማሪ ወጣቱ ጠበቃ አመሃ በድሉ ለቴዲ አፍሮ በዛሬው ዕለት በችሎቱ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የችሎት ውሎውን ተከታትለን ሙሉ ዘገባ ለማቅረብ እንሞክራለን።
- ኢትዮጵያ ዛሬ



