ምርጫ ቦርድ፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ እገዳውን ካሳለፉት አመራሮች ሦስቱ

ምርጫ ቦርድ (ዓርማ)፣ ከኦነግ ሊቀመንበርነታቸው የታገዱት አቶ ዳውድ ኢብሳ (በቀኝ)፤ እገዳውን ካሳለፉት አመራሮች ሦስቱ (በግራ)

ከኦነግ የተለያዩ አካላት በቀረበለት አቤቱታ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ እሰጣለሁ አለ

ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 9, 2020)፦ በኦነግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ከተለያዩ የፓርቲው አካላት ሲደርሱት በነበሩት አቤቱታዎች ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታወቀ።

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ስለመታገዳቸውና በሌላ ስለመካታቸው ምርጫ ቦርድ አውቆ እንዲያጸድቅላቸው እና አቶ ዳውድ እርሳቸውን አግደናል ያሉዋቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አግጃለሁ የሚሉ አቤቱታዎች የቀረቡለት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የቀረቡለትን አቤቱታዎች ሲመረምር መቆየቱንም አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ከሁለቱም ወገኖች የተመረጡና የቦርዱ ባለሙያዎች አጣርተው በሚያቀርቡት ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ቦርዱ ዛሬ ዓርብ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የቦርዱ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) አመራር አባላት የቀረበለትን አቤቱታዎች አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራር አባላት የአመራር ለውጥ እና እገዳን አስመልክቶ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲደርሱት እንደነበር ይታወቃል።

በአንድ በኩል በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በቁጥር 06/ABO/12 እና 7/08/12 05/03/19 በቁጥር 08/ABO/12 በተጻፉ ሁለት ደብዳቤዎች የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፓርቲው ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የእግድ ውሳኔ አስተላልፏል ሲሉ ለቦርዱ በማሳወቅ፤ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል አቶ ዳውድ ኢብሳ በ08/10/2020 (እ.ኤ.አ) በቁጥር 0211/xly/abo/2020 በተጻፈ ደብዳቤ፤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በኾኑት አቶ አራርሶ ቢቂላ፣ አቶ ቶሌራ ተሾመ፣ አቶ አቶምሣ ኩምሣ እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የኾኑት አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ አርብቾ ዲማ እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ ስለተወሰነ ይኸው ውሳኔ በቦርዱ እውቅና እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ በፓርቲው አባላት መኻከል የተፈጠረውን ያለመግባባት የሚያስረዱትን ከዚህ በላይ የተገለጹትን ደብዳቤዎችና ሌሎች የጽሑፍ አቤቱታዎችን መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ መርምሯል። በፖለቲካ ፓርቲ አባላት መኻከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባዔ የማቋቋም ሥልጣን አለው።

በመኾኑም በእነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመረጥ/የምትመረጥ አንድ፤ በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመረጥ/የምትመረጥ ሌላ አንድ፤ እንዲሁም እነዚህን ሁለት በባለጉዳዮቹ የሚመረጡትን ባለሙያዎች በሰብሳቢነት የሚመራ/የምትመራ ሌላ አንድ ባለሙያ ቦርዱ መርጦ በመመደብ የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ወስኗል። በዚህም መሠረት በሁለቱ አካላት እና በቦርዱ የተመረጡ ባለሞያዎች ጉዳዮን አጣርተው በሚያቀርቡት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ መኾኑን ያሳውቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ