ከ100 ሺህ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር የብር ኖት ለውጥ የጊዜ ገደብ ተጠናቀቀ

ዶ/ር ይናገር ደሴ (በግራ)፣ አቶ አሕመድ ሺዴ (መኻል) እና ዶ/ር ቀንአ ያደታ (በቀኝ)
እስካሁን ከ96 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰራጭቷል
ሐሰተኛ የብር ኖት አታሚዎች እየተያዙ ነው
ከባንክ ውጭ ሲዘዋወር የነበረ 31 ቢሊዮን ብር ገቢ ተደርጓል
ኢዛ (ዓርብ ጥቅምት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 16, 2020)፦ እስካሁን በተካሔደው የብር ኖት ለውጥ ከ96 ቢሊዮን ብር በላይ መሰራጨቱንና ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ሲያትሙ ነበሩ የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።
ከ100 ሺህ ብር እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር የተሰጠው የአንድ ወር የብር መለወጫ ጊዜ ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. መጠናቀቁን አስመልክቶ በተሰጠ መግለጫ፤ ባለፉት 28 ቀናት ከ900 ሺህ በላይ አዲስ የሒሳብ አካውንቶች እንዲከፈቱ አስችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት በዛሬው መግለጫ፤ ከጥቃቅን ችግሮች በስተቀር የገንዘብ ኖቱ ለውጥ በአግባቡ እየተካሔደ መኾኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ፤ ባለፉት 28 ቀናት ብቻ ባንኮች ከ920 ሺህ በላይ አዳዲስ አካውንቶች እንደተከፈቱና ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ መግባቱን አመልክተዋል።
ከ100 ሺህ ብር እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር መጠን ያለውን ገንዘብ የመቀየሪያ ጊዜ በዛሬው ዕለት የተጠናቀቀ መኾኑንና ከነገ ጀምሮ ይህንን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ መቀየር እንደማይቻልም አስታውቀዋል።
የሐሰተኛ የብር ኖት ሥርጭትን በተመለከተ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀንአ ያደታ እንዳመለከቱት ደግሞ፤ ሐሰተኛ የብር ሕትመት ጋር ተያይዞ በአማራ፣ በቤንሻንጉል፣ በአዲስ አበባና በደቡብ ክልሎች አንዳንድ ምልክቶች የተስተዋሉ መኾኑን ነው። ኾኖም እነዚህ ምልክቶች የጸጥታ ግብረ ኃይሉ በጥምረት ባካሔደው ሥራ ድርጊቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ከሰሞኑ በተለይ በአማራ ክልል ማሽን በመትከል ሐሰተኛ የብር ኖት እያተሙ የነበሩ አባላት እስከነ ማሽናቸው ስለመያዛቸውም ጠቅሰዋል።
በዚህ የብር ኖት ለውጥ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ሚና የነበረው ሲሆን፤ የብር ኖቶቹን በማጓጓዝ ሒደቱ ላይ ውጤታማ ሥራ መፈጸሙም ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ በሰጡት ማብራሪያ፤ የገንዘብ ለውጡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲገባ ማስቻሉን ነው።
ይህም በመኾኑ የአገሪቱ መደበኛ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጤናማ በኾነ መንገድ እየተጓዘ መኾኑን አመልክተዋል። (ኢዛ)