Kebede Chane

አቶ ከበደ ጫኔ

ለሕወሓት ጁንታ ቡድን ምስጢር በማቀበል ተጠርጥረው ስለመኾኑ እየተነገረ ነው

ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 1, 2020)፦ ከቀድሞ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የኾኑትና በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመመደብ እስካሁን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ከበደ ጫኔ ከአገር ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ በጸጥታ ኃይሎች ተገታ።

እንደምንጮች ገለጻ፤ አቶ ከበደ ከአገር ሊወጡ ሲሉ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ውጭ አገር መውጣት እንዳይችሉ ክልከላ ተደርጎባቸው የተመለሱት በትናንትናው ዕለት ነው።

አቶ ከበደ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርነት እያገለገሉ እንደነበር የሚታወቅ ቢኾንም፤ ከአገር እንዳይወጡ ክልከላ የተደረገባቸው ለሕወሓት ጁንታ ቡድን ምስጢር በማቀበል ተጠርጥረው ስለመኾኑ እየተነገረ ነው። በዚህም ምክንያት ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርነታቸው እንዲነሱ መደረጉም ታውቋል።

አቶ ከበደ ከዚህ ኃላፊነታቸው ቀደም ብሎ የገቢዎች ሚኒስትር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር፤ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በአማካሪነት ማገልገላቸው ይጠቀሳል። ከዚህም ሌላ የአማራ ክልል የአስተዳደር ጸጥታ ኃላፊ ኾነው መሥራታቸው ይታወቃል።

ከለውጡ በኋላ ከሚዲያ ጭምር የራቁት አቶ ከበደ፤ በትናንትናው ዕለት ከአገር ሊወጡ የነበረው ከባለቤታቸው ጋር እንደነበር ታውቋል።

በአሁኑ ጊዜ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውና ከአገር እንዳይወጡ ከመከልከላቸው ውጭ እስካሁን የተወሰደባቸው እርምጃ የለም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ