ቴዲ አፍሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ተቀጠረ
የቴዲ አፍሮ ችሎት ሙሉ ዘገባ
“ማረጋገጫ የተሰጠው በዶክተሯ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ አይደለም። ፖሊስ በሰጠው ላይ ተመስርተን ነው” ኩባዊው ዶ/ር ላስፔርቶ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥቅምት ፮ ቀን ፳፻፩-2001 ዓ.ም. October 16, 2008)፦ የዕለቱ ችሎት የተቀጠረው ከሰዓት በኋላ በመሆኑ ችሎቱን ለመከታተል የፈለጉ በርካታ ሰዎች፣ ፍርድ ቤቱ የጠዋቱን ሥራ አጠናቆ ሳይዘጋ ግቢው መግባት ጀመሩ። ነገር ግን ፖሊስ የቻለውን ያህል ከግቢው ለማስወጠት የሞከረ ሲሆን፣ በግቢው በመዘዋወፈር ያመለጡ ችሎት ተከታታዮች ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ሲል ተሠልፈው ከነበሩት ጥቂቶቹ የመግባት ዕድል ሲያገኙ በርካቶች ከውጭ ቀሩ።
ታዋቂው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አሳፍራ ያመጣችው ነጭ ሚኒባስ ችሎት አደረሰችው። ሙሉ ጥቁር ሱፍ በነጭ ሸሚዝ ለብሷል፣ ጥቁር ጫማ ተጫምቷል፣ ቡኒ የፀኃይ መነጽርም አድርጓል። ማስታወሻ ደብተር የሚመስል ነጭ ወረቀቶች ከፕላስቲክ ውሃ ጋር ይዞ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላ የያዛቸውን ነገሮች ካወለቀው ኮት ጋር ወንበሩ ላይ አስቀመጠው።
የችሎት ታዳሚዎች ገብተው ከተጠናቀቁ በኋላ ስምንት ሰዓት ለመሆን 10 ደቂቃዎች ሲቀሩ በዳኛ መሐመድ ዑመር ችሎቱ ተሰየመ። ከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋ፣ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከጠበቃው ሚሊዮን አሰፋ ጋር መቅረቡ ተረጋግጦ ችሎቱ ተሰየመ። (ሁለተኛው ጠበቃ አቶ አመሃ በድሉ አርፍደው ችሎቱን ተቀላቅለዋል)
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሣምንት በዋለው ችሎት የሰጠውን የሠነድ ማስረጃ ዝርዝርን በተመለከተ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲመጡ በተከሳሽ አማካኝነት የተጠየቁት የሠነድ ማስረጃዎች ምን እንደሚያስረዱ እንዲቀርብ የታዘዘውን ጭብጥ ፍርድ ቤቱ መቅረቡን ካረጋገጠ በኋላ ዓቃቤ ሕግ “አልደረሰኝም” በማለቱ ያልደረሰው ምን እንደሆነ እንዲያብራራ ከተጠየቀ በኋላ “አሁን ደረሰኝ” ሲል መልስ በመስጠቱ፤ በተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ስም ያለውንና ለዕለቱ ቀጠሮ የተያዘበት የመዝገብ ቁጥር 62266 መታየት ጀመረ።
መዝገቡ የተቀጠረው ለመስከረም 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ለመቅረብ መጥሪያ ወስደው ያልቀረቡ ሦስት የመከላከያ ምስክሮች ታስረው እንዲቀርቡ በታዘዘው መሠረት፣ ፖሊስ አስሮ ያቀረባቸው ሲሆን፣ በአስተርጓሚ ምክንያት ሳይመሰክሩ የተመለሱትና በድጋሚ የቀረቡት የምኒልክ ሆስፒታል ኩባዊ ሐኪም ዶ/ር ለስፔርቶ ሞያ፣ የኩባ ኤምባሲ ከላካቸው አቶ ዘለቀ በቀለ ከተባሉ አስተርጓሚ ጋር ቀረቡ።
ባለፈው ሣምንት ከተከሳሽ ወገን ሆነው ለማስተርጎም ቀርበው የነበሩት አቶ አበራ እና አቶ ወንደሰን አስተርጓሚዎች ችሎት ቢቀርቡም የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ከኤምባሲ የመጡት አስተርጓሚ ብቻ ቢተረጉሙ ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጹ ሁለቱ ተርጓሚዎች ከችሎት ተሰናበቱ።
ሦስቱ ምስክሮችና አስተርጓሚው መሐላ ከፈጸሙ በኋላ በቅድሚያ ዶ/ር ላስፔርቶ ከጠበቃው ለሚቀርብላቸው ዋና ጥያቄ መልስ በመስጠት የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተነገራቸው።
በሲ.ኤም.ሲ. አፓርታማዎች ውስጥ እንደሚኖሩ የተናገሩት የ50 ዓመቱ ኩባዊ የምኒልክ ሆስፒታል ስፔሻሊስት ሐኪም ቀደም ሲል በዚሁ ችሎት የዓቃቤ ሕግ ምስክር በመሆን ቀርበው የሚያውቁ ቢሆንም ትናንት ደግሞ በደረሳቸው መጥሪያ መሠረት ለቴዲ አፍሮ የመከላከያ ምስክር ሆነው ቀረቡ።
ተከሳሹን ያውቁት እንደሆነ በአስተርጓሚያቸው አማካኝነት ሲጠየቁ ድምፃዊ መሆኑን ከማወቅ ውጪ በአካል እንደማያውቁት ገልጸው፣ ከሞያቸው ጋር በተያያዘ ፈርመው የሰጡትን ሰነድ እንዲያዩት ቢደረግ ሊያውቁት ይችላሉ ወይ? በሚል ጠበቃው ላቀረበላቸው ጥያቄ “አውቀዋለሁ” በማለታቸው በሳቸው ፊርማ የወጣውን የአስከሬን ምርመራ እንዲያዩ ተደረገ።
ሟች ደጉ ይበልጣል የሚባል ሰው ጥቅምት 23 ቀን ሞቶ፣ ጥቅምት 24 ቀን ምርመራ እንደተደረገለትና የምርመራው ውጤትም፣ በግራ ግንባሩ በኩል አደጋ የደረሰበት መሆኑ፣ በአንገቱ በኩል አደጋ እንደደረሰበት፣ በአደጋው ምክንያት የመላላጥ እና የመቁሰል፣ በቀኝ ክንዱ በኩል ስብራት እንደ ደረሰበት፣ በግራ እጁና ጀርባው በኩል እስከ ታችኛው አከርካሪው አካል ድረስ እንዲሁም በግራ እጁ እና በማጅራቱ በኩል ተመሳሳይ አደጋ የደረሰበት መሆኑን፣ በውስጥ አካላቱ ውስጥ በተደረገው ምርመራ የተፈጠረ ጉዳት እንደሌለ፣ የመተንፈሻና መገጣጠሚያ አካሎቹ የተሰበሩ መሆናቸውን እና በአንጀቱ አካባቢ የደም ስርጭት የነበረ መሆኑን፣ በደም ዝውውር ምክንያት የውስጥ አንጀቱ የተጎዳ መሆኑን የሕክምና ማስረጃው እንደሚያስረዳ ዶ/ሩ አብራሩ።
አንድ ሐኪም አስከሬን ባልመረመረበትና በአካል ተገኝቶ ባላረጋገጠበት ሁኔታ፣ ማስረጃ ፈርሞ መስጠት ይችላል ወይ? በሚል ከጠበቃው ጥያቄ ቀረበላቸው፤ “… በእኛ ሀገር ራሳችን በአካል ባልተገኘንበት ሁኔታ ማስረጃውን አንሰጥም፤ ማስረጃ የሚሰጠው በአካል ተገኝቶ ምርመራ ያደረገው ሐኪም ብቻ ነው” ሲሉ መልስ ሰጡ።
የሟቹን የአስከሬን ምርመራ ያደረጉትና ሟች ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ሞቶ በጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ምርመራው እንደተደረገለት የሚገልጸውን ማስረጃ የሰጡትን ዶ/ር እንደሚያውቋቸውና የእሳቸውን የእጅ ጽሑፍም ያውቁ እንደሆነ ተጠይው “አውቃለሁ” በማለታቸው የመጀመሪያውን አስከሬን ምርመራ ያደረጉት ዶ/ር የማስረጃ ውጤት እንዲያዩት ተደረገ።
ዶ/ር ላስፔርቶ የተሰጣቸውን የመጀመሪያዋ ዶ/ር የፈረመችበት እና እሳቸው ቀኑን አስተካከሉት የተባለውን ማስረጃ ተመልክተው “ማን የጻፋቸው ናቸው? የእጅ ጽሑፉ የእናንተ ነው ወይ?” በሚል ጥያቄ ቀረበላቸው።
ጽሑፉን የሚያዘጋጀው አስተርጓሚው እንደሆነና “ፈርሙ” ሲባሉ መፈረማቸውን ገለጹ። “አስክሬኑን የመረመሩት ሐኪም ባለሙያ ናቸው አይደሉም?” ለሚለው የጠበቃው ጥያቄ ምስክሩ ምላሽ እንዳይሰጡ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ቢያቀርብም፣ ተቃውሞው ተቀባይነት ባለማግኘቱ “ባለሞያ ናቸው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
“አስክሬኑ ሲመጣ በቦታው የነበሩት ዶ/ር ምርመራ አድርገው ግኝታቸውን ካሰፈሩ በኋላ እርሶ ይህን አስከሬን መርምረዋል ወይ?” ለሚለው የጠበቃው ጥያቄ “ምርመራ አላደረኩም” አሉ። “እንደዛ ከሆነ ቀኑን ለመቀየር ያስቻሎት ምክንያት ምንድነው?” ሲሉ ጠበቃው ጥያቄ አቀረቡ።
ዶ/ር ላስፔርቶ ማብራራት ጀመሩ፣ “… በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው አለኝ ሙያችን ሳይንሣዊ በሆነ መንገድ የሚተነተን ነው፣ ይሄንን ወረቀት ያዘጋጀው የሆስፒታሉ አስተዳደር ነው። እኔ በወቅቱ ለዕረፍት ኩባ ሄጄ ነበር፤ ስመለስ አስተዳደሩ ከፖሊስ ጋር በመሆን ተነጋግሮ ፖሊስ ተሳስቶብኛል ስላለ ይቀየርልኝ ብሏልና ይቀየርለት ብለው ባዘጋጁት ቀኑ የተቀየረ የአስክሬን ምርመራ ውጤት ላይ ፈረምኩ” ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ።
“ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ እናደርጋለን” ያሉት ምርመራ ምን ምን እንደሚያካትት እንዲመልሱ ከጠበቃው ተጠየቁ “… ምርመራ ስናደርግ ሟች የሞተበትን ጊዜ፣ ሟቹ የሞተባቸውን የተለያዩ ተጨማሪ ምልክቶች፣ ሟቹ ሊሞት የቻለባቸውን የአሟሟት ሁኔታዎች ጭምር ያካትታል …” የዶ/ር ላስፔርቶ መልስ ነበር።
ታዲያ ሟች የሞተበትን ቀንና ምክንያት በፖሊስ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ መቀየር ይቻላል? በሚል ከጠበቃው ጥያቄ ሲቀርብ፤ ዓቃቤ ሕግ ቢቃወምም ፍርድ ቤቱ ተቃውሞውን ባለመቀበሉ ምስክሩ መልስ ሰጡ “… ሊቀየር አይችልም። ፖሊስ በዕለቱ የራሱን ማስረጃ ሊሰጥ ይችላል፣ በኛ ሞያ ግን ማስረጃን ሊሰጥ የሚችለው በዕለቱ አስክሬን በመንካት የመረመረው ሐኪም ብቻ ነው። እንደ ባለሙያም ማረጋገጥ የምችለው አንድ ሰው ሞተ ብሎ የሞተበትን ቀን ማረጋገጥ የሚችለው ባለሞያው ብቻ ነው።” ሲሉ መልስ ሰጡ። ጠበቃውም “ጥያቄዬን ጨርሻለሁ” ሲሉ ተቀመጡ።
ዓቃቤ ሕግ ላቀረበላቸው የመስቀለኛ ጥያቄ ዶ/ር ላስፔርቶ የሰጡት ምላሽ ሲጠቃለል “… የሟቹ አስክሬን ሲመረመር በወቅቱ አልነበርኩም። ምርምራው በተደረገና ማስረጃው ከተሰጠ ከአንድ ዓመት በኋላ ለዕረፍት ከሄድኩበት ኩባ ስመለስ ምርመራውን ያደረጉት ዶ/ር ስለሌሉና ፖሊስ ቀደም ሲል የተሰጠው ማረጋገጫ ቀኑ እንዲቀየር የሆስፒታሉን አስተዳደር በመጠየቁ ተሠርቶ የመጣው የምርመራ ውጤት ላይ ፈረሜያለሁ። በወቅቱ ከፖሊስ መጣ የተባለውን ማስረጃ አልሰጡኝም። አላየሁትም አስከሬኑን የመረመሩት ዶክተር በሰጡት ሰርተፍኬትም ሆነ መዝገብ ላይ ሟቹ በ22/02/1999 ዓ.ም. ሞቶ በ23/02/1999 ምርመራ እንደተደረገለት ሲገልጽ፤ የተስተካከለው ሰነድ ላይ ፈርም አሉኝ ፈረምኩ። ፖሊስ በ23/02/1999 ዓ.ም. አስከሬን ወደ ሆስፒታል አስገባሁበት ያለው ሰነድ ከመዝገቡ ጋር ይያያዝ አይያያዝ የማውቀው ነገር የለም። ይህን ደሞ ባለፈው ፍርድ ቤት በመጣሁ ግዜ ተናጋሬያለሁ።” ሲሉ ምስክርነታቸውን አጠናቀቁ።
ዳኛ መሐመድ ዑመር የፍርድ ቤቱን የማጣሪያ ጥያቄ ለምስክሩ አቀረቡ፤ “አስከሬኑን የመረመሩት ሐኪም ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ እሳቸው በሌሉበት ለምንድነው ቀኑ እንዲቀየር የተደረገው? የማንን መረጃ መሰረት አድርጋችሁ ነው ቀኑን የቀየራችሁት? በዛን ግዜ ከሐኪሟ ጋር የነበረ ሰው ነበር?”
“ባለፈው በመጣሁ ግዜ እኮ ይህን ተናግሬያለሁ፤ ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው በዶክተሯ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ አይደለም። ፖሊስ በሰጠው ላይ ተመስርተን ነው” ሲሉ መልስ ሰጡ።
ታስረው እንዲቀርቡ ከተጠሩት ሦስት ምስክሮች መካከል ቀደም ሲል የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበረው ኮንስታብል ከበደ ወየሳ የመከላከያ ምስክር ሆኖ ቀርበ። (“ኮንስታብል” የፖሊስ ማዕረግ ነው)። ከጠበቃው ለቀረቡለት ጥያቄዎችም “… ከሚያዝያ ወር 1998 ዓ.ም. ጀምሮ የፖሊስ አባል መሆኑን፣ ለአራት ወራት ሥልጠና መውሰዱንና ከተመረቀበት ግዜ ጀምሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ እንደሠራ፣ አደጋው በደረሰበት ሰዓት ፊት በር አካባቢ ተመድቦ ይሠራ እንደነበረ ገለፀ።
ጠበቃው ጥያቄውን በማብቃቱ፤ ዳኛው የማጣሪያ ጥያቄዎችን አቀረቡ። “… አደጋው በደረሰበት ዕለት ከአንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ፊት በር በተባለው አካባቢ በምድብ ሥራው ላይ እንደነበር፤ አደጋውን ያደረሰው መኪና አይነት ለይተው ባያውቁትም አረንጓዴ የቤት መኪና እንደነበር ገልፆ፤ በመኪናውና በሱ መካከል የ20 ሜትር ያክል ርቀት እንደነበር መኪናውን ያሽከረክር የነበረው ማን እንደሆነ አለማየቱን አስረድቷል።
የተከሳሽ ጠበቃ ቀሪ ምስክሮችን የማይፈልጋቸው መሆኑን በመግለፁ ምስክሮቹና ሁለቱን አስተርጓሚዎች ችሎቱ አሰናብቷቸዋል።
ጠበቃው የተከሳሽን የመከላከያ ማስረጃ ስላጠናቀቀ የክርክር ማቆሚያ (እስካሁን ያደርጓቸው ክርክሮችና ማስረጃዎቻቸውን በሚመለከት የማብራሪያ ንግግር) አድርገው ውሳኔ እንዲሰጥ በመጠየቃቸው፤ መጀመሪያ ዓቃቤ ሕግ፣ ቀጥሎ ደግሞ ጠበቃው የክርክር ማቆሚያ ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል ተሰጣቸው።
ዓቃቤ ሕግ ፍቃዱ ፀጋ ባደረጉት ረዘም ያለ የክርክር ማቆሚያ ንግግር፤ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጥቅምት 23 ቀን ሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው፣ ፊት በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ደጉ ይበልጣል የተባለው ሟች መንገዱን ሲሻገር ቅድሚያ መስጠት ሲገባው ቅድሚያ ባለመስጠት ገጭቶ መሄዱን በመጥቀስ ክስ መስርተው ለክሱ ያስረዳልኛል ሲሉ ከቆጠሯቸው ምስክሮች ሦስቱን ማሰማታቸውንና ስድስት የሰነድ ማስረጃዎችን ማቅረባቸውን፣ አንዱ የዓይን ምስክር ቀርቦ የምስክርነት ቃሉን ባይሰጥም ለፖሊስ የሰጠው ቃል ተያይዞ መቅረቡን አስረድቷል።
ፖሊስ ካቀረባቸው ምስክሮች፤ አንዱ ምስክር ኮድ 2-59868 የሆነው የተከሳሹ አረንጓዴ የቤት መኪና በሁለት ላዳ ታክሲዎች መካከል ፍጥነት ጨምሮ እየበረረ ሲመጣ ፊት በር አካባቢ ወደ አስፋልት ሲሻገር የነበረውን ሟች ገጭቶ ወደ ካዛንቺስ በኩል ሲያመልጥ ተከታትሎ ታርጋ መያዙን፣ ሌላኛው ምስክር ደግሞ ከሼራተን አካባቢ ሲመጣ መኪናው ፍጥነት እንዲቀንስ መንገሩን እና በጓደኛው ጥሪ መጥቶ የተገጨውን ሰው ማየቱን፣ ተገጪው ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሕይወቱ ማለፉን፤ አራተኛው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሟቹ በወደቀበት ቦታ ተገኝተው ፕላን ማንሳታቸውንና በፕላኑ ላይ ገጪው ለእግረኛ ቅድሚያ ሳይሰጥ መግጨቱን ማረጋገጡን፣ የምኒልክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራም ምኒልክ ሆስፒታል በስህተት ያሰፈረው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን የማጣራት ሂደት በራሱ ማድረጉን፤ ዶ/ር ላስፔርቶን አስቀርቦ የሰነዱን ትክክለኛነት ማጣሩቱን በመግለጽ ማስረጃዎቹን ክሱን በሚገባ እንዳስረዱለት ተዘርዝሯል።
የተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች የዓቃቤ ሕግን ከሰሙ በኋላ ሆን ብለው የተዘጋጁ መሆናቸውን፤ የነበሩበት ቦታ፣ ሰዓት እና የተደዋወሉት ስልክን በሚመለከት ምስክርነት ሲሰጡ አንዱ ከአንዱ ጋር የተምታታ ሃሳብ ማቅረባቸውን በመግለጽ ተከሳሹ ክሱን በሚገባ ስላልተከላከለ “ጥፋተኛ” እንዲባልለት ጠይቋል።
የተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጠበቃ በክርክር ማቆሚያ ንግግራቸው “… ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በመጀመሪያ ላመጣው ክስ የቀረበው 1ኛ ምስክር ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ በ7 ሰዓት ላይ ተመድቦ ይጠብቅበት የነበረው ፊት በር አካባቢ አንድ ጥቁር አረንጓዴ መኪና በሁለት ታክሲዎች መካከል በከፍተኛ ፍጥነት መጥቶ አስፋልቱ ላይ ወድቆ በነበረው ልጅ እግር ላይ ሄዶበት ሲያመልጥ፤ ከነበረበት 20 ሜትር ርቀት ላይ ሮጦ በመሄድ 5 ሜትር ያህል ሲቀረው እንደ ደረሰበት እና ታርጋውን እንደፃፈ በኋላም ጓደኛው ሲመጣ ወድቆ የነበረው ልጅ ሕይወቱ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሲያልፍ ለፖሊስ ማመልከታቸውን ሲገልጽ፤
“ሁለተኛው ምስክር ሟች በቀኝ ጠርዝ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ በማቋረጥ ላይ እያለ አንድ ጥቁር አረንጓዴ መኪና ገጭቶት መሄዱንና ልጁ መውደቁን ገልጾ መስክሯል። እነዚህ ሁለት ፖሊሶች በአንድ ቦታ ላይ ነበርን ብለው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ አንዱ “በወደቀበት ሄደበት”፤ ሲል ሁለተኛው ደግሞ “ገጭቶ ጣለው” በማለት ሁለት የተለያየ የምስክርነት ቃል ሰጥተዋል።
“በሌላ በኩል እነዚህ ሁለት ምስክሮች በሁለት ላዳ ታክሲዎች መካከል በፍጥነት በማሽከርከር ገጭቶ መሄድ ምን ማለት እንደሆነና ፍጥነት የነበረውን መኪና ከ20 ሜትር ርቀት ላይ በመድረስ በጨለማ ውስጥ ታርጋ ማየት ምን ማለት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ ይውሰድልን” ሲሉ ጠበቃው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ፖሊስ በዋና ኢንስፔክተር ቴዎድሮስ በቀለ ፊርማና በፖሊስ ሕጋዊ ማኅተም፤ ለፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ተከሳሹን ለምርመራ ለማቆየት ግዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት የፖሊስ ደብደቤ እንደሚያስረዳው፤ … በተለምዶ ፊት በር አካባቢ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ የመከላከያ ፖሊስ አባላት አንድ የሰሌዳ ቁጥሩ ያልታወቀ መኪና ሰው ገጭቶ ሲያመልጥ መመልከታቸውንና ከመኪናው ኋላ እየተከተለ የነበረን ላዳ ታክሲ ተከትሎ ታርጋውን ይዞ እንዲመጣ ልከውት እያለ ባለታክሲው ተመልሶ በመምጣት ታርጋ ቁጥር ሰጥቷቸው መሄዱንና ነገር ግን ስሙንም ሆነ አድራሻውን ባለማስቀመጡ መቸገራቸውን በመግለጽ ይህንን ባለታክሲ እስኪያገኙና ምርመራቸውን እስኪያጠናቅቁ ግዜ እንዲሰጣቸው የጠየቁበትን በሕጋዊ ፖሊስ ማኅተም የተደገፈ ደብዳቤ እያነበቡ ይህንኑ ማስረጃ በሰነድ ማስረጃቸው ላይ ማያያዛቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የፕላን ማስረጃ በሚል የቀረበው የሰነድ ማስረጃ ላይ ለግዜው ሠሌዳው ያልታወቀ መኪና ገጭቶ ማምለጡን በግልጽ መስፈሩን፤ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ክስ ሲመሰርት እና ምስክር ሲያሰማ ፖሊሶቹ ታርጋውን ማየታቸውንና መኪናው በሁለት ላዳዎች መካከል ሆኖ መግጨቱን እንዲያስረዱ መደረጉ ፍጹም ሐሰት እና ሊታመን የማይችል ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ማስረጃ ነው ብለውታል።
በተጨማሪም ሟች በ22/02/1999 ዓ.ም. መሞቱንና በ23/02/1999ዓ.ም በምኒልክ ሆስፒታል ምርመራ እንደተደረገለት የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ ከክሱ ጋር አያይዞ ክስ ከመሰረተ በኋላ ሰነዱ ሲደርሰን ተከሳሹ በተጠቀሰው ዕለት በከተማው ውስጥ እንዳልነበረ በመግለጽ ተቃውሞ በማቅረብ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ስንጠይቅ የለም ማስረጃዬን አሻሽላለሁ በማለት ከሕግ ውጪ ከአንድ ዓመት በፊት የተሰጣቸውን ማስረጃ እንደገና አስተካክሎ ሲያመጣ ሰነዱ ውድቅ እንዲደረግልን ላቀረብነው ጥያቄ መልስ ሳይሰጠን ፍርድ ቤቱ ምኒልክ ሆስፒታል ማብራራሪያ እንዲሰጠው ጠይቆ እኚሁ ምስክር ቀርበው እንዲመሰክሩለት አድርጓል ብሏል።
ምስክሩ ከቀረቡ በኋላ ዓቃቤ ሕግ በዋና ጥያቄያቸውም ሆነ በመስቀለኛ ጥያቄ እየደጋገሙ “በተለምዶ የቀን ስህተት ሲፈጠር ታስተካክላላችሁ አታስተካክሉም?” በማለት የአስከሬን ምርመራውን ለማረም በዋና መዝገብ ላይ ያልተበላሸንና ትክክለኛ ማስረጃን ማስቀየር ልምድ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ሞክረዋል፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ፍትሃብሔር ሕግ አንድ ሰው “ሰው” የሚባለው ከተወለደበት እስከ ሞተበት ባለው ቀን ሆኖ እያለ እነዚህን ቀናት በሕግ ተረጋግጦና ዳኞች ተሰብስበው በሚያጸኑት ውሳኔ ብቻ ሊቀየር የሚችል ሆኖ እያለ በልማድ ዋና መዝገቡ ሊቀየር ይችላል ማለታቸው፤ ልማድም ሆነ እየተሠራበት ካለ ሕገወጥ ሥራ ነው በማለት ጠበቃው ተናግረዋል።
ዞሮ ዞሮ በምኒልክ ሆስፒታል ዋና መዝገብ ላይ ያለው አስክሬኑን የመረመሩት ሐኪም ያረጋገጡት እና አሁን ቀርበው የመሰከሩት ምስክር እንደገለጹት፤ ትክክለኛው የአስከሬን ምርመራ ተደርጎ የሚወሰደው በራሱ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለተከሳሽ የደረሰው በዋና አስክሬን መርማሪ ሐኪሟ የተሰጠው ሰነድ እንደሆነ አስረድተዋል።
ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁንም አዲስ አበባ የገባው በጥቅምት 23 ቀን መሆኑን በመግለጽ ለዚህም በቂ ማስረጃ አቅርቧል ብለዋል።
በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ተከሳሹ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው መኪና ሲያሽከረክር እንደነበር ሲገልጽ የቆየ መሆኑ ከመግለጽ ውጭ መንጃ ፍቃድ ሳይኖረው ስለማሽከርከሩ አንዳችም ማስረጃ ያላቀረበ መሆኑን በወንጀል ክርክር ደግሞ ተከሳሹ መንጃ ፍቃድ እንደሌለው የሚያስረዳ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ መከላከያ ለማቅረብ እንደማይገደዱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የተሽከርካሪውን ደህንነት ከ13 ቀናት በኋላ የመረመሩት ኢንስፔክተር በመከላከያ ምስክርነት ሲቀርቡ፤ በመኪና በመግጨት የሰው ሕይወት ያጠፋ መኪና ማስረጃዎች በአቧራ፣ በውሃና በጤዛ እንዳይጠፉ በአስቸኳይ ምርመራ እንደሚደረግ የገለጹ ሲሆን፣ “የተከሳሹ መኪና ለምን ወዲያውኑ አልመረመራችሁም?” በሚል ጥያቄ ሲቀርብ “ተከሳሹን በወቅቱ ስላላገኘነው ነው” የሚል መልስ ሰጥተዋል። ነገር ግን ተከሳሹም አደጋው ደረሰ ከተባለበት ማግስት ማለትም ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደ ነበር የራሱ የፖሊስ ማስረጃ ያስረዳል ብለዋል።
የተጠቀሱት ማስረጃዎች በሙሉ በመዝገቡ ላይ የተያያዙ መሆናቸውን ጠበቃው ጠቅሰው ማስረጃዎች የሚያሳዩት “ተከሳሹ ሰው ገሏል ተብሎ ክስ እንዲመሰረትበት የተወሰነ ቆይቶ ነው” ካሉ በኋላ፤ ዓቃቤ ሕግ የቆጠራቸው ምስክሮች ሲመሰክሩ መኪናው ገጨውና በእግሩ ላይ ሄደበት ያሉ ሲሆን፣ የሐኪም ማስረጃው ደግሞ ሟቹ በመላው የሰውነት አካሉ ላይ አደጋ እንደደረሰበት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። ስለዚህም ፍርድ ቤቱ የቀረቡትን ማስረጃዎች በሚገባ መርምሮና አገናዝቦ ተከሳሹን ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) በነፃ እንዲያሰናብትላቸው ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም የቀሩትን ማስረጃዎች መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት በቂ ግዜ የሚያስፈልገው መሆኑን ገልጾ፤ ከ18 ቀናት በኋላ ለሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ዳኛው ቀጠሮ ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ባቀረበው የመከላከያ ማስረጃ ክሱን አልተከላከለም ካለ “ጥፋተኛ ነህ” በማለት የሚወስንበት ሲሆን፤ የቀረበው የመከላከያ ማስረጃ ክሱን በሚገባ ተከላክሏል ካለ ግን በዕለቱ በነፃ ያሰናብተዋል።
ከስድስት ወራት ከ23 ቀናት የእስር ቆይታ በኋላ ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ቤተሰቦች፣ አድናቂዎችና ለራሱ ለቴዲ አፍሮ ተናፋቂ ቀን ስትሆን ዕለትዋን ደግሞ የኀዘን አልያም የደስታ ሆና እንድታልፍ የዳኛውን ውሳኔ ትጠብቃለች።



