Ambassador Dina Mufti

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የኢትዮጵያና የሱዳን ውዝግብ ለቀጠናው ሰላም ሥጋት መኾኑ ተገለጸ

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 24, 2021)፦ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የገባው እና በኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውስጥ ከወራት በላይ የቆየው የሱዳን ጦር ወደ ቀድሞው ይዞታው ከተመለሰ ብቻ ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ከሱዳን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ስለመኾኗ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ ገለጻቸው ላይ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ድርድር የሚካሔደው ሱዳን ወደ ቀድሞ ይዞታዋ ከተመለሰች ነው።

በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረቶች ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወቅታዊ አቋም ጉዳዩን በሰላም መፍታት ስለመኾኑ የሚያመለክተው የቃል አቀባዩ መግለጫ፤ ከሱዳን ጋር ድርድር የሚደረገው ግን ሱዳን ከኢትዮጵያ ድንበር ወጥታ ወደነበረችበት ስትመለስ መኾኑን ያስታወቀችበት ኾኗል። በዚሁ ጉዳይ ላይ አምባሳደር ዲና በሰጡት ተጨማሪ ገለጻ፤ የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ከድርጊቱ ይታቀብ ብለዋል። በሱዳን ድርጊት መጠቀም የሚፈልግ ሦስተኛ ወገን መኖሩንም በመጥቀስ፤ ይህም ለቀጠናው ሰላም ሥጋት መኾኑንም በዚሁ መግለጫቸው ላይ አብራርተዋል። በሌላ አንጻር ሱዳን በአካባቢው አገሮች ተወረርኩ በማለት እየገለጸች ነው።

በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ያለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቱርክ ያላትን ፍላጐት ያሳወቀች መኾኑ አይዘነጋም። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ለመደራደር ወታደራዊ ክንፏ የኢትዮጵያ ድንበር ለቆ ወደነበረበት መመለስ አለበት ወደሚለው አቋም የተገባ ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ያለመግባባት ለመፍታት እናደራድር የሚሉ አገሮች ያሉ ሲሆን፣ ይህ ጥያቄያቸው ተገቢ ስለመኾኑ ያስረዱት አምባሳደር ዲና፤ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው ቅድመ ሁኔታ ግን መጠበቅ ያለበት ስለመኾኑ ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቱርክ እና በሕንድ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋርም በተካሔደ ውይይት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመከረበት ሲሆን፣ በተለይም ትግራይን መልሶ በማቋቋም ዙሪያና የኢትዮ ሱዳን ድንበር ሁኔታን የማስረዳት ሥራዎች ስለማከናወናቸው አምባሳደሩ ከሰጡት መግለጫ ለመገንዘብ ተችሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ