የመደመር መንገድ

አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጽሐፍ፤ “የመደመር መንገድ”

“መደመር” የሚለው መጽሐፍ ሁለተኛው ክፍል ነው
መ ጽሐፉ በዋናነት የለውጡን ሒደት የሚያሳይ ነው

ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 6, 2021)፦ የለውጡን ፈለግ እና መደመር ያለፈበትን መንገድ እንደሚዳስስ የተነገረለት “የመደመር መንገድ” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈው አዲስ መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ። ክፍል ሁለት የሚል ርዕስ ባይሰጠውም፤ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉትና “መደመር” የሚል ርዕስ የነበረው መጽሐፋቸው ሁለተኛው ክፍል እንደኾነ ታውቋል።

የለውጥ ሒደቱን ከመነሻው ጀምሮ የሚያትተውና በሪፎርም (ለውጥ) ጉዞው የተፈጥሩ መልካም እድሎች እና ፈተናዎች ጭምር የያዘ ነው የተባለው ይህ መጽሐፍ ዛሬ ሽያጩ ተጀምራል። መጽሐፉ ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ታሪኮችን አጠቃሎ የያዘ ነው ተብሏል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቆዩ ታሪካቸውን ያመላከቱበት ሲሆን፤ መጽሐፉን ጽፎ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት መፍጀቱ ተነግሯል።

በዚህ መጽሐፍ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በፌስቡክ ገጻቸው፤ “ይህ 'የመደመር መንገድ' የተሰኘ መጽሐፍ፣ የለውጡን ፈለግ እና መደመር ያለፈበትን መንገድ ወደ ኋላና ወደ ፊት፣ መለስ ቀለስ እያለ ይዳስሳል። በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰውን ለውጥ የወለዱ አስተሳሰቦች ምን እንደኾኑ፣ ከጥንስሱ ጀምሮ የሪፎርም ጉዞው ምን እንደሚመስል፣ በሒደት የተፈጠሩ መልካምና ፈታኝ አጋጣሚዎች እንዲሁም ተጓዳኝ ታሪኮችን ይዟል። ከዛሬ ነገ እጽፋቸዋለሁ እያልኩ ሳልጽፋቸው፣ በልቤ ሰንዱቅ እንደታሸጉ ለረጅም ዘመናት አብረውኝ የቆዩ ትዝታዎቼ እና ከጓዶቼ ጋር የተጋራኋቸው ወዳጃዊ ሐሳቦች ጭምር ተካትተውበታል። በብዙ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ። ቀደም ሲል ለወጣው መጽሐፍ እንደ ተከታይና አስረጂ ኾኖ እንዲያገለግል ዘርዘርና ሰፋ ብሎ፣ ከመጠነኛ የአጻጻፍ ቅርጽ ለውጥ ጋር የተሰናዳ መጽሐፍ ነው።

“በዝግጅት በኩል ሲታይ መጽሐፉ ሁለት ዓመታትና ከዚያ በላይ የኾነ ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ የተጀመረበት ወቅት ከዚያኛው የመደመር መጽሐፍ ቢቀድም እንጂ አይዘገይም። ልክ እንደ በፊቱ በሁለት ቋንቋዎች፣ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ተሰናድቶ የሕትመት ሥራው ስለተጠናቀቀ ነገ አንባቢ እጅ ይደርሳል።” ብለው ነበር። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ