Ararsa Bikila and Dawud Ibsa

አቶ አራርሳ ቢቂላ (በግራ) እና አቶ ዳውድ ኢብሳ (በቀኝ)

የእጩዎች ምዝገባ በመጠናቀቁ ምርጫ ቦርዱ ከፈቀደ እሳተፋለኹ ብሏል

ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 17, 2021)፦ በሁለት ቡድኖች ተከፍሎ ሲወዛገብ የቆየውና በዘንድሮ ምርጫ መሳተፍ አለመሳተፉን ለማወቅ አስቸጋሪ የኾነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንደኛው ቡድን ምርጫ ቦርድ ቀን ካራዘመልኝ ወደ ምርጫው (ምርጫ 2013) በመግባት ልወዳደር እችላለሁ ማለቱ ተሰማ።

ሰሞኑን አዲስ ሊቀመንበር መምረጡን ያስታወቀው የኦነግ ቡድን ዛሬ አስታወቀ በተባለው መረጃ፤ ራሱን ከምርጫ ማግለል የማይፈልግ መኾኑን ነው። ሰሞኑን በተካሔደው የጠቅላላ ጉባዔ፤ አቶ አራርሳ ቢቂላን አዲስ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠው እና 43 ቋሚ እና 5 ተለዋጭ የመካከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ጉባዔውን ማጠናቀቁን የገለጸው ኦነግ፤ በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት ያለው መኾኑን አስታውቋል። ነገር ግን የእጩዎች ምዝገባ የተጠናቀቀ በመኾኑ ምርጫ ቦርዱ ከፈቀደ ወደምርጫው እንገባለን ማለታቸው ተሰምቷል።

ከዚህ ቡድን ጋር በተቃራኒው የቆመውና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ፤ የሰሞኑን ጠቅላላ ጉባዔ የተቃወመ ሲሆን፤ በዘንደሮው ምርጫ እንደማይሳተፍ ከገለጸ ሰነባብቷል። በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳየው የኦነግ ቡድንም ቢኾን፤ ከዚህ ቀደም በተለይ አሁን የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር በመኾን የተመረጡት አቶ ቀጄላ መርዳሳ፤ ኦነግ በምርጫው የመሳተፍ እድሉ አጠራጣሪ መኾኑን ገልጸው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።

በሌላው መረጃቸው ደግሞ፤ በውስጥ ችግራቸው ምክንያት የምርጫ ዝግጅት ባለመደረጉ፤ የእጩ ማቅረቢያ ቀኑ እንዲራዘምላቸው እንደሚጠይቁ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። በዛሬው ዕለት ደግሞ ዝርዝር መረጃ ባያካትትም አቶ ቀጄላ ያሉበት የኦነግ ቡድን ምርጫ ቦርድ ከፈቀደ ምርጫ እንገባለን የሚል አንደምታ ያለውን መረጃ ተላልፏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ