ኦነግ በምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ውሳኔ ተቃወመ
አቶ አራርሳ ቢቂላ (በግራ) እና አቶ ዳውድ ኢብሳ (በቀኝ)
ኦነግ ፍትሕ እንደሚሻና ፓርቲውን ከአገሪቱ የፖለቲካ ሒደት ለማስወጣት የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቆመ
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 29, 2021)፦ በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈበትን ውሳኔ ተቃወመ።
በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመራው ቡድን ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ምላሽ፤ በቅርቡ ያካሔደው ጠቅላላ ጉባዔ ፍትሐዊ ነው ብሎ እንደሚያምን እና የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበል የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገልጸዋል።
ጠቅላላ ጉባዔውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት የተካሔደ መኾኑን ያስታወሱት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ምርጫ ቦርድ በኦነግ ውስጥ መከፋፈል እንዳለ እና አቶ ዳውድ ኢብሳ እንቢ ማለታቸው እየታወቀ፤ ሁለት ሦስተኛ አልተገኘም ብሎ የሰጠውን ውሳኔ ተቃውመዋል።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔን የተቃወሙት አቶ ቀጄላ፤ ፓርቲያቸው ፍትሕ የሚሻ መኾኑን ገልጸው፤ ኦነግን ከአገሪቱ የፖለቲካ ሒደት ለማስወጣት መፈለጉንም በመጠቆም፤ ማንኛውንም ሥራ እንታገላለን ስለማለታቸው የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ ያካሔደው ጠቅላላ ጉባዔን የተሟላ ያለመኾኑን፤ ከጉባዔው አባላት ሁለት ሦስተኛው አልተገኙም በሚል እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉን ባወጣው መግለጫ አስታውቆ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። በዚሁ መግለጫው ላይ በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ በምርጫ 2013 ለመወዳደር ያቀረበውንም ጥያቄ ምርጫ ቦርዱ ውድቅ አድርጎታል። (ኢዛ)



