ዶክተር ፋና ሃጐስ

ዶክተር ፋና ሃጐስ፣ አዲሷ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

አዲሷ ተሿሚ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት እና ዓቃቤ ሕግ ነበሩ

ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 15, 2021)፦ የቀድሞዋ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሃጐስ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በመኾን እንዲያገለግሉ ተሾሙ።

የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሠር ክንዲያ ገ/ሕይወት በኃላፊነት ቦታቸው ላይ ካለመገኘታቸው ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲው ያለ ፕሬዝዳንት የቆየ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጠባባቂ ፕሬዝዳንትነት እየተመራ ነበር ተብሏል።

ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ግን ዶክተር ፋና ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነት እንዲያገለግሉ ተሹመዋል። ዶክተር ፋና ይህንን ኃላፊነት ከመቀበላቸው ቀደም ብሎ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሥርዓተ ጾታ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር እና የሕግ እና ሥነመንግሥት ኮሌጅ ዲን በመኾን ማገልገላቸው ተጠቅሷል።

ዶክተር ፋና በትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ዓቃቤ ሕግ በመኾንም የሠሩ ሲሆን፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ12 ዓመታት የሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሠር በመኾን እንደሠሩ ተገልጿል።

በትምህርት ዝግጅታቸውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፍሪ ስቴት እና ዋርዊክ ያገኙ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከኬንያው የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚ አግኝተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!