“አማራን መግደልና ማሳደድ ይቁም!”

”በተለያዩ አካባቢዎች በአማሮች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም”፣ "አማራን ማሳደድ ይቁም”፣ "ሕጻናትን መግደል እና ከተማ ማፍረስ ጀግንነት አይደለም”፣ ”በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃትና መፈናቀል መንግሥትን ሊያሳስበው ይገባል”

አጣየ ከተማ በመውደሟ ነዋሪው በድንኳን እየገባ ነው
ሰልፎቹ ሰላማዊ ቢኾኑም አንዳንድ ያልተገቡ ሁኔታዎች መታየታቸውን የአማራ ክልል ኃላፊ ገለጹ

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 21, 2021)፦ ከሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የተካሔዱ ሰልፎች መንግሥት የዜጐችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲያስጠብቅና በዘርና በማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ መልእክት የተላለፈበት መኾኑን የአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ገለጹ።

ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ፤ እስካሁን ሰልፉ በተደረጉባቸው ከተሞች በርካታ ሰዎች የተገኙበት እንደነበር አስታውሰዋል። የሰልፎቹ ዓላማ በአማራ ክልልና አማራ በሚኖርበት አጐራባች አካባቢ በአጠቃላይ አማራ ላይ እየደረሰ ያለ ጥቃትን የሚያወግዝ ይዘት ያለው ነው። በተለይ ደግሞ በቅርብ በሰሜን ሸዋ አጣየና አካባቢው ላይ በደረሰው በጣም ዘግናኝ ጉዳት እና እንዲህ ያሉትን ጥቃቶች የሚያወግዙ ሰልፎች እንደነበሩ አክለዋል ገልጸዋል።

በጣም ክቡር የኾነው የሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት የለበትም። በተለይ አማራ በማንነቱ መሳደድ የለበትም፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ መጠበቅ አለበት፣ ጥቃቱ መቆም አለበት ብሎ ለመንግሥት መልእክት ያስተላለፉበት እንደኾነም ዳይሬክተሩ በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።

መንግሥት የዜጐቹን ደኅንነት ይጠብቅ፣ ሞት መቆም አለበት፣ በጋራ ኾነን ጥቃትን እንከላከል የሚል ይዘት ያላቸው መልእክቶች በዋናነት የተላለፉበት ነበርም ብለዋል። ሰልፈኞቹ ኀዘናቸውን የገለጹበት ጭምር መኾኑንም ገልጸዋል። ሰልፎቹ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቃቸውንም ወጣቶቹ ይዘውት ከተነሱት ዓላማዎች ጋር የሚጋጩ መልእክቶችና ያልተገቡ ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው አመልክተዋል። ይህንንም “ሰልፎቹ በአብዛኛው በሰላማዊ ሁኔታ የተጠናቀቁ ናቸው ይባል እንጂ፤ አንዳንዶቹ መልእክቶች ሰብእናን የሚነኩ፣ ስምም እየተጠራ ሰዎች የሚሰደቡባቸው ነበሩ፤ ይህ ብቻ አይደለም በዚህ ዓመት ምርጫ እናካሒዳለን፤ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መኾን አለበት።” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ ብቻ ነው አማራ ክልልም ኾነ ሌላው ክልል እንዲሁም ይህ ሕዝብ የሚጠቀመውት የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።

ይሄ ኾኖ ሲያበቃ ግን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የአንዳንድ ፓርቲዎችን ሎጐዎችን አውርዶ መቅደድና ማቃጠሉም ጥሩ ነገር አለመኾኑንና እንዲህ ያለው ድርጊት ለማንም የማይጠቅም መኾኑን በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

እንዲህ በማድረግ የሚመጣ መፍትሔ እንደሌለም ያመለከቱት አቶ ግዛቸው፤ ይህንን በማድረግ አማራን ልንታደገው የማይችል ስለመኾኑም አስገንዝበዋል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ካልታረሙ፤ ጥሩ ነገር ሊኾን አይችልም የሚል ምልከታቸውን ያንጸባረቁት ዳይሬክተሩ፤ እንዲህ ያሉ ወጣ ያሉ ነገሮች እንዳይከሰቱ የበለጠ ማኔጅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ፍላጐትን በየትኛውም መንገድ ስንገልጽ በሰላማዊ መንገድ መኾን መቻል አለበት የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

”በተለያዩ አካባቢዎች በአማሮች ላይ የሚፈጸም ግድያ ይቁም”፣
“አማራን መግደልና ማሳደድ ይቁም!”

የዳይሬክተሩ የዛሬ መግለጫ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የአጣየና አካባቢውን ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡበት ነበር። የአጣየና አካባቢው እየተረጋጋና የሸዋ ሮቢት አካባቢ ነዋሪዎች ደግሞ ወደነበሩበት እየተመለሱ ስለመኾኑ አመልክተዋል።

አሁን ላይ ያለው ሁኔታ በርዶ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ የተመጣ መኾኑንና ተኩስም መቆሙን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን አካባቢ ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል። ነገር ግን የአጣየ ከተማ በመውደሙ ሰው ሊመለስ አይችልም ምክንያቱም ሰው ንብረቱም፣ ሀብቱም፣ ቤቱም የወደመ ስለኾነ እነዚህ ነዋሪዎች በተለየ ማስተናገድ ግድ ብሏል። እነዚህን ዜጐች በድንኳን በመጠለል እርዳታ ማቅረብ ተጀምሯል። በተለይ ደብረ ብርሃን አካባቢ ድንኳን በመጣል ከጥቃቱ የተረፉ ዜጐችን የዕለት እርዳታ የማቅረብ፣ አልባሳትና ምግብ የመስጠት፣ ሕክምና የመስጠት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ዘርና ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃቱን በመቃወምና መንግሥት ጥቃቱን ያስቁም የሚል ገንፍሎ በየአደባባይ የወጣው ሰልፈኞች በተለያዩ ከተሞች እየወጡ ሲሆን፤ ዛሬም በደብረ ብርሃን ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ስሜቱን እና ተቃውሞውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጿል።

ከሰሞኑ በቁጣ በመውጣት በአደባባይ ስሜታቸውን የገለጹ የአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ማርቆስ ይገኙባቸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ