Ethiopian Human Rights Council

ኢሰመጉ (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ)

መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ታጥቆ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ባለው ቡድን ላይ ሕጋዊ፣ አስቸኳይ እና የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ኢሰመጉ ጠይቋል

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 21, 2021)፦ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተፈጸመ ያለው የሰዎች ሞት፣ አካል መጉደል፣ መፈናቀል እና በአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ዋስትና ያጡባት አገር መኾኗን በመጥቀስ፤ በአገሪቱ ላይ የተደቀነው ችግር በእጅጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ገለጸ።

ኢሰመጉ በዚህ ባወጣው መግለጫ ላይ ካሰፈራቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ፤ “በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸመው ጥሰት አድማሱን ከማስፋቱና ወደሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ሰዎችን ለእልቂት ከመዳረጉና አገራችንን አዘቅት ውስጥ ከመክተቱ በፊት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች በአገራችን ሰላም ስለሚወርድበትና የሰብአዊ መብቶች ዋስትና ስለሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመክሩና መፍትሔ እንዲያበጁ” የሚለው አንዱ የመፍትሔ ሐሳብ ነው።

ከዚህም ሌላ መንግሥት የጸጥታ አካላትን ኃይል በአስቸኳይ በማጠናከር በሕገወጥ መንገድ ታጥቆ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ባለው ቡድን ላይ ሕጋዊ፣ አስቸኳይ እና የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች እንዲሁም ሕዝብን ለመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡትን በአስቸኳይ ተጠያቂ በማድረግ የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ጠይቋል።

የጸጥታ ሥጋት ያለባቸውን እንዲሁም መሰል ጥቃቶች ሲፈጸምባቸው የነበሩ በአገራችን የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን በመለየት ለነዋሪዎች የተለየ ጥበቃ የሚደረግበትን ስልት በአፋጣኝ በመዘርጋት ተግባራዊ እንዲያደርግ እንዲሁም በጥቃቱ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ መሠረተ ልማቶች በአፋጣኝ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲያደርግ፤ እና ቁሳዊ እንዲሁም አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ መልሶ እንዲያቋቁም ኢሰመጉ ዳግም አሳስቧል።

ኢሰመጉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ያወጣው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በማስቆም አገርን እንታደግ (አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ)

ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ፡- ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ይፋ በማውጣት መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ሲወተውት የነበረ መኾኑ ይታወቃል፡፡

በተለይም በቅርብ ጊዜ ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መግለጫውን ባዘጋጀበት ወቅት ባወቀው ልክ አሳውቆ ጥሰቶቹ ከመባባሳቸው በፊት መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ ካልኾነ ተጠያቂነት የማይቀር መኾኑን ገልጾ ማሳሳቡ ይታወሳል፡፡ ኾኖም ግን በአገራችን ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰና እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ ሰብአዊ መብቶች ምንም ዋስትና የላቸውም ማለት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

በዚህም በአጣየ ከተማና አካባቢው ስለተፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ኢሰመጉ ከዚህ ቀደም ባወጣው ልዩ መግለጫ እንዲሁም በቅርቡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም. ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረጉና ምክረ-ሐሳቦችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ኾኖም ግን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ፤ እንዲሁም አካባቢው የጸጥታ ሥጋት እንዳለበት ታውቆ፤ አስፈላጊው ጥንቃቄ መወሰድ ሲገባው ከሚያዝያ 6/2013 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በከባድ መሣሪያ የታገዘና ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሰዎችን ለሕልፈት፣ ለንብረት ውድመት እንዲሁም ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡

ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በአጣየ ዙሪያ ባሉት ማለትም በማጀቴ፣ በቆሪ ሜዳ፣ በዙጢ፣ በዩሎ ቆላ፣ በሙሉ በርጊቢ፣ ካራ ቆሬ፣ ኔጌሶ፣ ኩሪቱሪ እና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁና ከባድ መሣሪያ በታጠቁ ኃይሎች ተኩስ ተከፍቶ፤ በማጀቴ በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን፣ በካራ ቆሬ የጸጥታ ኃይሎች መቁሰላቸውን፣ ነዋሪዎች አካባቢዎቹን ለቀው ወደሌላ የገጠር ቀበሌዎች መሰደዳቸውንና ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን እንዲሁም አጣየ፣ ቆሪሜዳ፣ ዙጢ፣ ካራቆሬ የተባሉ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ እንደወደሙ ኢሰመጉ ከአካባቢው የሰበሰበው መረጃ ያመላክታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሸዋ ሮቢት ከተማ ወደ ደሴ የሚወስደው መንገድ ከሚያዝያ 07/2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተሸከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ሰዎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ ይገኛል፡፡

ከዚህም ሌላ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች እንደሚገደሉ፣ የገበሬ ቤቶችና የእህል ጎተራ እንደሚቃጠል እንዲሁም ሰዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ኢሰመጉ በየጊዜው ከሚሠራቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ለመረዳት ችሏል፡፡

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ነዋሪው አሁንም ለችግር መጋለጡንና አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሁንም ያልተሻሻለና እንደልብ ለመንቀሳቀስ ምቹ እንዳልኾነ ከቦታው ለኢሰመጉ የቀረቡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ሰዎች በሕገወጥ ታጣቂዎች እንደሚገደሉ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን በጉማይዴና አማሮ ልዩ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች፣ እንደሚገሉ፣ የአካል ጉዳት እንደሚደርስባቸው እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ እንደሚታሰሩ ለኢሰመጉ አቤቱታዎች ቀርበዋል፡፡ በተመሳሳይ በአፋር ክልል በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያና የንብረት ውድመትም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ ማሳያ ነው፡፡

በዚህም ኢሰመጉ ከላይ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አስመልክቶ ምርመራ እያደረገ የሚገኝና ግኝቱን ይፋ የሚያደርግ መኾኑን እያሳወቀ፤ እስከዛው ግን ድርጊቶቹ በምንም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌላቸውና የሚወገዙ መኾኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

በዚህም አገራችን በተለያዩ አቅጣጫዎች ሰዎች የሚሞቱባት፣ አካል የሚጎድልባት፣ የሚፈናቀሉባት እና ንብረት የሚወድምባት፤ በአጠቃላይ ሰብአዊ መብቶች ዋስትና ያጡባት አገር ኾናለች፡፡ የድርጊቶች አፈጻጸምም ኾነ አዝማሚያው አገራችን ላይ የተደቀነውን ትልቅ ችግር አመላካች በመኾኑ የአገራችን ቀጣይ እጣ ፋንታ ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ስለኾነም መንግሥት ድርጊቱን መከላከልና ማስቆም ስላልቻለበት ምክንያት እንዲሁም ስለቀጣይ እርምጃዎቹ ይፋዊ ማብራሪያ እንዲሰጥ ኢሰመጉ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ሰዎች ሐሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በሚገልጹበት ጊዜ እስር፣ ወከባ እንዲሁም መሰል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ያሳስባል፡፡

የመፍትሔ ሐሳብ

በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸመው ጥሰት አድማሱን ከማስፋቱና ወደሌሎች አካባቢዎች ተዛምቶ ሰዎችን ለእልቂት ከመዳረጉና አገራችንን አዘቅት ውስጥ ከመክተቱ በፊት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች በአገራችን ሰላም ስለሚወርድበትና የሰብአዊ መብቶች ዋስትና ስለሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመክሩና መፍትሔ እንዲያበጁ፤

መንግሥት የጸጥታ አካላትን ኃይል በአስቸኳይ በማጠናከር በሕገወጥ መንገድ ታጥቆ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ ባለው ቡድን ላይ ሕጋዊ፣ አስቸኳይ እና የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ፣ የድርጊቱን ፈጻሚዎች እንዲሁም ሕዝብን ለመጠበቅ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡትን በአስቸኳይ ተጠያቂ በማድረግ የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ፤

የጸጥታ ሥጋት ያለባቸውን እንዲሁም መሰል ጥቃቶች ሲፈጸምባቸው የነበሩ በአገራችን የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችን በመለየት ለነዋሪዎች የተለየ ጥበቃ የሚደረግበትን ስልት በአፋጣኝ በመዘርጋት ተግባራዊ እንዲያደርግ እንዲሁም በጥቃቱ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ መሠረተ ልማቶች በአፋጣኝ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲያደርግ፤ እና

ቁሳዊ እንዲሁም አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ በማድረግ መልሶ እንዲያቋቁም ኢሰመጉ ዳግም ያሳስባል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ