Ethiopian Election 2021

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ምርጫ 2013)

እስከዛሬ የደረሱትን እንደሚያስተናግድና ለዚህም ምክንያቱ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ላይ በመኾኑ ነው ሲል አስታውቋል

ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 6, 2021)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተወዳዳሪ እጩዎችን የመተካት፣ የመቀየር፣ የመለወጥ እና ማንኛውንም ዐይነት ተያያዥ ማሻሻያዎችን እንደማይቀበል አስታወቀ።

እስካሁን ለቀረቡለት ከእጩዎች ለውጥ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን ግን የሚያስተናግድ መኾኑን የገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ግን እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን የማያስተናግደው የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ላይ በመኾኑ ነው ሲል አስታውቋል።

የምርጫ 2013 የእጩዎችን መቀየርን አስመልክቶ ቦርዱ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ የተሰጠ መረጃ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመቀበል፣ ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም የድምፅ መስጫ ወረቀት ቅደም ተከተል ሎተሪን በማከናወን የእጩዎችን ዝርዝር አጠናቆ ለድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት ሲያዘጋጅ ቆይቷል።

በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 39 (3) የፖለቲካ ፓርቲ እጩውን መለወጥ ወይም መተካት የሚቻልበት ቀን የእጩ ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ ካለቀ በኋላ ከኾነ ከድምፅ መስጫው ቀን ከአንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደኾነ ይደነግጋል። በዚህም መሠረት ከዛሬ ከሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የእጩ መተካት፣ መቀየር፣ መለወጥ እና ማንኛውንም ዓይነት ማሻሻያ የማይቀበል መኾኑን ይገልጻል።

እስከአሁን የቀረቡ ከእጩዎች ለውጥ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች የሚስተናገዱ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሕትመት እየተከናወነ በመኾኑ እና በሕግ የተቀመጠውም ግዴታ በማብቃቱ፤ ከእጩዎች ምዝገባ ጋር የተገናኘ ማንኛውንም ዐይነት አቤቱታ መቀበል ማቆሙን ፓርቲዎች ተረድተው ከዚህ በፊት ያስገቧቸው የለውጥ ጥያቄዎችን ብቻ እንዲከታተሉ እናስታውቃለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ