ለመራጭነት 28 ሚሊዮን ዜጎች ተመዝግበዋል
እስካሁን የተመዘገቡት መራጮች 28,731,935 በመኾናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን እስከ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. አራዘመ
የመራጮች ምዝገባ ለሁለተኛ ጊዜ ተራዘመ
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 7, 2021)፦ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 እስካሁን የተመዘገቡ የመራጮች ቁጥር ከ28 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተገለጸ። የመራጮች ምዝገባ ለተጨማሪ ሰባት ቀናት (አንድ ሳምንት) እንዲራዘም መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ አስታወቀ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል። (ኢዛ)
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ዋና ተግባር የኾነው የመራጮች ምዝገባን እያከናወነ እንደኾነ ይታወቃል። በዚህም ሒደት በመጀመሪያ ሰሞን የነበረው የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ፤ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በተሰበሰበው መረጃ (ያለፉት ሦስት ቀናትን ሳይጨምር) 28,731,935 ያህል መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፤ የመራጮች ምዝገባ በ 41,798 ያህል ምርጫ ጣቢያዎች እየተከናወነ ይገኛል።
የመራጮች ምዝገባ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በተጨማሪ ለ15 ቀን ተጨምሮ ከአፋር እና ከሶማሌ ክልሎች ውጪ የማጠናቀቂያ ጊዜው በዛሬ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚኾን ማሳወቁ ይታወሳል። በዚህ ወቅትም፤
1. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት ተደራራቢ የበዓላት ቀናት መኖራቸው እና በዚያም የተነሳ በሕጉ መሠረት ብሔራዊ በዓላት ዝግ በመኾናቸው የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን አለመቻሉን፤
2. የመራጮች ምዝገባ በተራዘመበት ወቅት 1500 መራጮች የመዘገቡ ጣቢያዎቸን ለይቶ ንዑስ ጣቢያዎችን የማደራጀት ሒደት ጊዜ መውሰዱን፤ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የመራጮች መጨናነቅ ምርጫ ጣቢያ ላይ መፈጠሩን ተረድቷል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመራጮች ካርድ በመውሰድ መምረጥ የሚችሉ ቀላል የማይባሉ ዜጎች በዚህ የተነሳ የመራጮች ካርድ አለመውሰዳቸውን ቦርዱ በመገንዘብ ባደረገው ስብሰባ፤ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሐረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል የመራጮች ምዝገባ እስከ ዓርብ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ለተጨማሪ 07 ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።
በዚህም መሠረት በእነዚህ የከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች የሚገኙ መራጮች የመራጭነት ካርዳቸው በእነዚህ ቀናት በአቅራቢያቸው በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እንዲወስዱ እያሳወቅን፤ የቦርዱ አስፈጻሚዎች እና አስተባባሪዎች በሕጉ መሠረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ እናስታውቃለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም.



