European Union Flag

የአውሮፓ ሕብረት ባንዲራ

የጋራ ምክር ቤቱ የአውሮፓ ሕብረት ጥያቄን ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ብለውታል

ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 8, 2021)፦ በአማራ ክልል በምርጫ ጉዳዮች አብሮ ለመሥራት የጋራ ምርጫ ምክር ቤት ያቋቋሙት የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአውሮፓ ሕብረት፤ ምርጫውን ለመታዘብ የኮምዩኒኬሽን መሣሪያ ይዤ ይግባ፣ ከምርጫ ቦርድ በፊት መግለጫ ልስጥ ብሎ ያቀረበው ጥያቄ የአገር ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ነው አለ።

የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የአውሮፓ ሕብረት ምርጫውን ለመታዘብ በተለይ በምርጫው ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ በፊት መግለጫ ልስጥ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ የቦርዱን ሥልጣን የሚጋፋና የአገርን ሉዓላዊነት በእጅጉ የሚዳፈር ኾኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል።

ከዚህም ሌላ ሕብረቱ ምርጫውን ለመታዘብ የቴሌኮምዩኒኬሽን መሣሪያ መጠቀም ይፈቀድልኝ ብሎ ያቀረበውም ጥያቄ ያልተገባ ስለመኾኑ የገለጸው የጋራ ምክር ቤቱ መግለጫ፤ ይህ ጥያቄው ከአገር ሉዓላዊነት ነፃነት ጋር የሚጋጭ መኾኑን አመላክቷል።

የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ ቀደም የተካሔዱትን የይስሙላ ምርጫዎች እንዳልታዘበ ሁሉ፤ አሁን ከቀድሞ በአንፃራዊነት የተሻለ ድባብ ያለው ምርጫ በሚካሔድበት ወቅት ምርጫውን አልታዘብም ማለቱንም ኮንኗል።

የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ የሚወዳደሩ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቋቋመ ሲሆን፤ የጋራ ምክር ቤቱን የመሠረቱት የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሕብረት፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ ብልጽግና ፓርቲ፣ ሕብር ኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ኢዜማ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄና እናት ፓርቲ እንደኾኑ ይታወቃል። በዚህ ውስጥ አብን ያልተካተተ መኾኑን መዘገባችን ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ