በአማራ ክልል በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋቋሙ
አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ፣ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ኾነው የተመረጡት የአማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ናቸው
አብን አልተካተተም
ኢዛ (እሁድ ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 25, 2021)፦ በቀጣዩ ምርጫ 2013 በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ኾነው ለመፍታት እና ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የጋራ ምክር ቤት ማቋቋማቸውን እና ምክር ቤቱ ሥራ መጀመሩን አስታወቁ። በዚህ ምክር ቤት አብን አልተካተተም።
የጋራ ምክር ቤቱን ማቋቋማቸውን ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ያስታወቁት የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራት ሕብረት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ብልጽግና ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው።
በዘጠኙ ፓርቲዎች የተቋቋመው ምክር ቤት ለምርጫው ፍትሐዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተአማኒነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ተደጋግፎ ለመሥራት ችግር ካለም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል እንደሚኾን ተገልጿል።
ምርጫው ሰላማዊና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የተገለጸው ይህ ምክር ቤት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እርስ በእርስ ከመጠራጠር እና ከመጠላለፍ ተላቅቀው የሠለጠነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል።
በዚህ ምክር ቤት ውስጥ በአማራ ክልል ውስጥ ከብልጽግና ቀጥሎ በርካታ ተወዳዳሪዎችን አቅርቧል ተብሎ የሚታመነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በዚህ ምክር ቤት ውስጥ አልተካተተም። አብን በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ለምን እንዳልተካተተ የተገለጸ ነገር የለም።
ይህንን የጋራ ምክር ቤት የአማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ሰብሳቢ ኾነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል። (ኢዛ)



