Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD)

ታላቁ የህዳሴ ግድብ

ከወደ ግብጽ አስደማሚ ዜና ተሰምቷል

ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 19, 2021)፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሒደት 80 በመቶ በላይ መድረሱንና ከሲቪል ሥራው ደግሞ 91.8 በመቶ መጠናቀቁ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በነበረው የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃ 80 በመቶ መድረሱን ነው።

በዕለቱ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ከተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው 54.4 በመቶ፣ የሃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራው ደግሞ 55.2 በመቶ ስለመድረሱ ተጠቅሷል።

ግድቡ ሁለተኛውን የውኃ ሙሌት በክረምቱ ወራት የሚያከናውን ሲሆን፤ ወቅቱን ጠብቆ የሚከናወን ስለመኾኑም በዛሬው ዕለት በተደረገው ውይይት ላይ ማረጋገጫ ተሰጥቷል።

በክረምቱ የሚካሔደው የውኃ ሙሌት 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የሚያዝበት ሲሆን፤ ይህም አምና የተደረገውን የውኃ ሙሌት ጨምሮ ግድቡ በክረምቱ ወቅት የሚይዘው 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይደርሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ከወደ ግብጽ የተሰማው የህዳሴውን ግድብ የተመለከተ መረጃ ለየት ያለ ኾኗል። ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተሰማው ዜና፤ ሁለተኛው ዙር የህደሴው ግድብ የውኃ ሙሌት የግብጽ ፍላጐት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማያሳርፍ መኾኑን የሚያመለክት ነው።

ይህንን የገለጹት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሱክሪ ሲኾኑ፣ አክለው ያመለከቱትም ግብጽ በአስዋን ግድብ ያላት የውኃ ክምችት መተማመን የፈጠረላት መኾኑ ነው።

ግብጽ ከመጀመሪያው የግድቡ የውኃ ሙሌት በግብጽ ላይ የውኃ እጥረት ይፈጥራል በሚል የውኃ ሙሌቱን አጥብቃ ስትቃወም የነበረች በመኾኑና ዛሬ ደግሞ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርብኝም የማለቷ ጉዳይ ነገሩን አስደማሚ አድርጐታል።

ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግድቡን ሒደት በተመለከተ በተደረገ ውይይት ላይ ጐልተው ከወጡት ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት ሒደት ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችን፣ የኦፕሬሽን እና የውኃ አለቃቀት ሒደቶችን ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማትቀበል መኾኑን ያሳወቀች መኾኑ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ