ምርጫ 2013 ሰኔ 14 እንደሚካሔድ ተገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ምርጫ 2013)
• በሐረር እና በሱማሌ ክልሎች ሰኔ 14 ምርጫው አይካሔድም
• በምርጫ ምዝገባ አቤቱታ የቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ምርጫው በዕለቱ አይካሔድም
ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፲፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 20, 2021)፦ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚካሔድና የምርጫ ሒደቱም የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሚካሔድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
እንደ ቦርዱ መግለጫ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ አቤቱታ የተነሳባቸው እና ምዝገባውን ዘግይተው የጀመሩ እንዲሁም ያላጠናቀቁ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ላይ ግን በዚሁ ቀን አይካሔድም።
የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ እንደገለጹት፤ ቦርዱ ባጋጠመው የዝግጅት መጓተት ምክንያት የምርጫ ጊዜውን ለማራዘም ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ድምፅ መስጫ ቀኑ እንዲሻሻል ተደርጓል።
ከዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት እንደተቻለው አቤቱታ የቀረበባቸው እና ጉዳያቸው በፍርድ ሒደት ላይ ያሉ ተብለው እና ሰኔ 14 ቀን ምርጫ ከማይካሔድባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሐረሬና የሱማሌ ክልሎች ይገኙባቸዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሔድ አቅዶ የነበረው ግንቦት 28 ቀን እንደነበር አይዘነጋም። (ኢዛ)



