ነገ ይተላለፋል የተባለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለምልልስ እንዳይተላለፍ ታገደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ፎቶ፣ ምርጫው ሁለት ቀን ሲቀረው በፋና ቴሌቭዥን ሊተላለፍ የነበረው ቃለምልልስ ማስታወቂያ ላይ የተነሳ ስክሪንሾት)
ቃለምልልሱ ሊተላለፍ የነበረው ምርጫው ሊጀመር 57 ሰዓታት ሲቀሩት ነበር
ቃለምልልሱ ከምርጫው በፊት አይተላለፍም
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 17, 2021)፦ ነገ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በፋና ቴሌቭዥን ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ይተላለፋል ተብሎ እየተዋወቀ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቃለምልልስ እንዳይተላለፍና ማስተዋወቃቸውን እንዲያቆሙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን አሳሰበ።
ከምርጫ 2013 በፊት ያለው አንድ ሳምንት የጥሞና ጊዜ በመኾኑ ፓርቲዎችም ኾኑ እጩ ተወዳዳሪዎች ምንም ዐይነት ቅስቀሳ ማድረግ የማይችሉበት መኾኑን በማውሳት በርካቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃለምልልስ ማስታወቂያ ተመልክተው ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ከነዚህም ውስጥ አንዱ የኾኑት የኢዜማው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት፤ በምርጫ ሕጉ መሠረት የአንድ እጩ ቃለምልልስ በጥሞና ጊዜ ውስጥ በቴሌቭዥንም ኾነ በመገናኛ ብዙኀን እንዳይተላለፍ የሚጠይቅ ነው።
ይህንንም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን የገዥው ፓርቲ እጩ በፋና ቴሌቭዥን ያደረጉት ቃለምልልስ በጥሞና ጊዜ ውስጥ እንዳይተላለፍ በማገድ ለምርጫው ፍትሐዊነት የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ እጠይቃለሁ በማለት ቃለምልልሱ እንዳይተላለፍ ጠይቀዋል።
የምርጫው ቅስቀሳ ካበቃ እና የጥሞና ጊዜው ከተጀመረ በኋላ ለገዥው ፓርቲ እና ለአንድ እጩ የተለየ እድል የሚሰጥ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተላለፍ ቃለምልልስ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው መኾኑንም በዚሁ የትዊተር መልእክታቸው ላይ አስፍረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቃለምልልስ ከምርጫ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም ብዥታ እንዳይፈጠር ሲባል የመገናኛ ብዙኀን ከምርጫው በፊት እንዳያስተላልፉና ማስተዋወቃቸውንም ያቁሙ” በማለት ማሳሰባቸው ታውቋል። (ኢዛ)