”የወያኔ መሪዎች የትግራይን ህዝብ አይወክሉም” ፕ/ት ኢሣያስ አፈወርቂ
70 ደቂቃ የፈጀውን የቲቪ ቃለምልልስ ይዘናል
Ethiopia Zare (ረቡዕ ግንቦት 19 ቀን 2001 ዓ.ም. May 27, 2009)፦ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ለስዊድን ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለምልልስ፤ ”የወያኔ/ኢህአዲግን መሪዎች ጥቂቶችና የየትኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ/ብሔር ውክልና የሌላቸው ናቸው። የትግራይ ህዝብንም አይወክሉም።” ብለዋል። በዚሁ ቃለምልልስ ላይ ሲ.አይ.ኤ.ን፣ አሜሪካንን፣ ስዊድንን እና ወያኔ/ኢህአዲግን ወንጅለዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ከስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዶናልድ ቡስትረም (በተለይ ለስዊድን ቴቬፊራ / ቲቪ4) በአስመራ ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግሥት በእንግሊዝኛ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ፤ ከወያኔ/ኢህአዲግ ጋር ምንም ዓይነት መልካም ግንኙነት ወደፊት እንደማይኖራቸው ገልፀዋል። ፕ/ት ኢሣያስ፤ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ግንኙነትና ወዳጅነት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ቀድሞ ወደነበረበት ሠላማዊና ጤናማ ግንኙነትና ወዳጅነት እንደሚቀየር እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
”... ወያኔ/ኢህአዲግ ምንም እንኳን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የትግሬ ነው ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም፤ የትግራይ ህዝብ ሙሉ ውክልና የሌለው ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፤ ... አማራ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ትግሬ፣ ... በማለት ህዝቡን ከፋፍለውና አጋጭተው እየገዙ ያሉት የትኛውንም የኢትዮጵያ ህዝብ የማይወክሉ ጥቂት ወገኖች ናቸው። እነዚህ ወገኖች በውስጥ ከፈጠሩት ችግር በተጨማሪ ከውጭም ችግሮችን በመፍጠር ከውጭ ኃይሎች በሚያገኙት ድጋፍ የሥልጣን ዕድሜቸውን ለማራዘም የሚጥሩ ናቸው። ...” በማለት በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ የገለጹት ፕ/ት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ በዚህም ምክንያት የድንበር ማካለሉን ተግባራዊ እንዳይሆን እየጣሩ የሚገኙት የአዲስ አበባ ገዥዎች በሶማሊያም ጣልቃ ገብነታቸውም በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርጉት ጥረት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤርትራ በአሁኑ ጊዜ የተረጋጋችን ሠላማዊ ሀገር እንደሆነች የገለጹት ፕ/ት ኢሣያስ፣ ከጎረቤት ሀገሮቻቸው ጋር የድንበር ግጭትና ውጥረት ከሌለባቸው ከጆሃንስበርግ፣ ከናይሮቢ፣ ከሌጎስ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ ሁኔታ ኤርትራ ሠላምና መረጋጋት የሰፈነባት ሀገር ናት ብለዋል።
በኤርትራ የነዳጅና የወርቅ ማዕድንን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኤርትራ በሚቀጥለው ዓመት ነዳጅ ማውጣት እንደምትጀምርና ለዚህም የውጭ ሀገር ኩባያዎችና ኢንቨስተሮችን ጨምሮ እንደሚሳተፉ ገልፀዋል። በዚህ ሥራ ላይ ካናዳዊ፣ የደቡብ አፍሪካና የጀርመን ኩባንያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፣ ወርቅ ብቻውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ይቀይረዋል ብለው እንደማያምኑና ለውጡን ለማሳመርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እነኝህን ማዕድናት በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የኤርትራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ምን እንደሚመስል ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዶናልድ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ”የፖለቲካ ሥርዓታችን ከስዊድን እጅግ ይሻላል” ሲሉ መልሰዋል። ይህንንም ሲያስረዱ ስዊድን በዓለም ላይ ጥሩና የተሻሉ ሀገሮች ከሚባሉት ውስጥ ብትሆንም፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሀብት 10 በመቶ በማይሞላው ህዝብ ውስጥ የሚገኝ ነው። ምናልባት በስዊድን የኑሮው ደረጃና ጥራት ከዚምባብዌ ትሻል ይሆናል እንጂ፤ በህዝቡ ውስጥ ባለው የሀገር ሀብት ስርጭት ግን ኤርትራን አትበልጣትም ብለዋል።
የስዊድናዊ እና ኤርትራዊ ዜግነት ስለለውና ባለፉት ስምንት ዓመታት በኤርትራ በእስር ላይ ስለሚገኘው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ ሁኔታ የት እንደታሰረ፣ ፍርድ ቤትስ ይቀርባል ወይ? ምን ዓይነት ወንጀል ነው የሠራው? ... ተብለው የተጠየቁት ፕ/ት ኢሣያስ፤ ”የት እንዳለና ምን እንደሠራ የእኔ ጉዳይ አይደለም፤ በእሱ ላይ ጊዜዬን ማባከን አልፈልግም። ... ከፍተኛ ጥፋት ሠርቷል፣ ለሱም ተጠያቂ ነው። ... ስለሠራው ወንጀልም ላወራህ አልፈልግም። ... ከእስር አንለቀውም። ፍርድ ቤትም አናቀርበውም። እንዴት አድርገን ጉዳዩን እንደምንይዘው እኛ እናውቃለን። በራሳችን መንገድ እሱንና እሱን የመሳሰሉትን ጉዳያቸውን እንዴት እንደምንይዝ እናውቃለን። ... በዚህ ጉዳይ ላይ ከነጭራሹ ከስዊድን ጋር አንደራደርም፤ ምን እንደምናደርግም አንወያይም። በጭራሽ!” ብለዋል።
በዚሁ ቃለምልልስ ላይ በኤርትራ ውስጥ የግል መገናኛ ብዙኀን አልነበረም፣ አሁንም የለም ሲሉ ፕ/ት ኢሣያስ ተናግረዋል። ጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅ የ44 ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ ከመስከረም 13 ቀን 1994 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 23 ቀን 2001 እ.ኤ.አ.) በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
የጋዜጠኛ ዳዊት ይስኃቅን ጉዳይ አስመልክቶ የስዊድን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኳታር በኩል ኤርትራን ሊያግባባ መሞከሩን የጠቀሱት ፕ/ት ኢሣያስ፤ የኳታር ሰዎች ኤርትራዊ ዜግነት እንኳን እንዳለው ከኤርትራ ማወቃቸውን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ ይህንን ያደረጉት ኤርትራ ከኳታር ጋር ወዳጅ ነች በሚል እምነት እንደሆነ አክለው ገልጸዋል።
ፕ/ት ኢሣያስ ከስዊድን ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዲኖራችሁ ነው የምትፈልጉት? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ”በአሁኑ ወቅት ከስዊድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረን አንፈልግም። አይኖረንም። ... ለእኔ የስዊድን መንግሥት አግባብ፣ ሥርዓት የለሌውና ያልሠለጠነ ነው። ...” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚሁ ቃለምልልስ ላይ በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብ መሃከል ስላለው ግንኙነት፣ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ስላለው ፓርቲ፣ በድንበሩ ዙሪያ ስለሠፈረው የኤርትራ ጦር፣ አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ስላላት አቋም፣ ስሲ.አይ.ኤ.፣ ስለ ስዊድን፣ ... በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተውበታል።
የፕ/ት ኢሣያስን ቃለምልልስ የዘገበው የስዊድኑ ቲቪ4፣ በዛሬና በትናንት ዜና ሥርጭቱ፤ በስዊድን ጥገኝነት የጠየቁና ከሀገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ወደ 300 የሚጠጉ ኤርትራውያን ከስዊድን የመባረራቸው ትዕዛዝ መሰረዙን የስዊድን ኢሜግሬሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጠቅሶ ዘግቧል። በትናንትናው ዕለትም የጥገኝነት ጥያቄዋ ተቀባይነት ያገኘችውን ወጣት ሣባን ቃለምልልስ አድርጎላታል። ሣባ ከሀገር እንድትባረረ የስዊድን ኢሚግሬሽን ወስኖባት ነበር። በተለይ ይህ የፕ/ት ኢሣያስ ቃለምልልስ የስዊድን ባለሥልጣናትን ያበሳ እንደሆነ ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለማረጋገጥ ችሏል። ፕ/ት ኢሣያስ የስዊድን መንግሥት የአሜሪካንን ጭራ የሚከተል ነው ሲሉ በቃለምልልሱ ላይ ገልጠዋል።
ፕ/ት ኢሣያስ አፈወርቂ በተለይ ለስዊድን ቴቬፊራ (ቲቪ4) ከጋዜጠኛ ዶናልድ ቡስትረም ጋር በእንግሊዝኛ ያደረጉትንና የሰባ ደቂቃ ቃለምልልስ ከዚህ በታች ባለው ቪዲዮ ላይ የማጫወቻ ቁልፉን በመጫን ማየትና ማድመጥ ይችላሉ።
ፕ/ት ኢሣያስ አፈወርቂ በሜይ 2009 እ.ኤ.አ. ”ቢዝነስ ዊክ” ከተሰኘውና መሠረቱን ቻይና ካደረገው መጽሔት ጋርም ቃለምልልስ አድርገዋል። ይህንኑ ቃለምልልስ በቪዲዮ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ!