ግርማ ካሣ (ጥቅምት 3 ቀን 2002 ዓ.ም.) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በዚህ በያዝነው የኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት (2002 ዓ.ም.) የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው። በተለይም የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አሥራት ጣሴ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዙሪያ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ትንሽ እሳትን እንደለኮሰ እያየን ነው። (ኢንጂነር ግዛቸው እሳቱን ለማጥፋት ቢሞክሩም)

 

በውጭ ሀገር ካሉ የአንድነት ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ የፓልቶክ ክፍል ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚሰጡት አስተያየቶችና በየድረ ገጾች የሚጻፉ ጽሑፎች የሚያመለክቱት ነገር ቢኖር፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በታሰረችበት ሁኔታ ወደ ምርጫው መግባት ትልቅ ተቃውሞን ሊያስነሳ እንደሚችል ነው።

 

በሀገር ቤትም ተመሳሳይ ሁኔታ ያለ ይመስላል። የአውራምባ ታይምሱ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ላቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም ሲመልሱ “ብርቱካን የአንድነት ሊቀመንበር ነች። መሪያችን ነች። ስለዚህ እሷን ከሌሎች ሰዎች ጋር አናያትም። በመሪነቷ፣ በእናትነቷና በመሥራችነቷ ለብቻዋ ነው የምንመለከታት። እና እርሷን እስር ቤት አስገብተን ምርጫ ሊኖር አይችለም የሚል አስተሳሰብ እና አቋም ነው ያለን” ነበር ያሉት።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችው ለአንድ ዓላማ ነው። እርሱም በኢትዮጵያ ሕግ የበላይ ሆኖ፣ የዜጎች መብት ተከበሮ፣ በነፃነቷና በአንድነቷ ታፍራና ተከብራ የምትኖር አንዲት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመመስረት ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከሁሉም በላይ የርሷ መታሰር ሳይሆን የሚያሳስባት፣ የታሰረችበት ዓላማ ከግቡ የመድረሱና ያለመድረሱ ጉዳይ ነው እንጂ። ይህማ ባይሆን ኖሮ መጀመሪያውኑ እውነትን ሰርዛ፣ ያልሆነውን ሆነ ብላ አገዛዙ የጠየቃትን አሟልታ አለመታሰር ትችል ነበር።

 

እስቲ ትንሽ አዕምሯችንን እንዲጫር አንዳንድ ጥያቄዎችን ላቅርብ። እርስ በርስ ሳንስማማና አንድነት ሳይኖረን፣ ዝም ብለን ወደ ምርጫው ብንገባ ምን የምናመጣው ለውጥ አለ? በእውኑ አቶ አሥራት ጣሴ እንዳሉት አሁን ባለው አሳዛኝ የፖለቲካ ሁኔታ ምርጫውን አሸንፈን ብርቱካን ሚደቅሳና ማስፈታት እንችላለን?

 

በሀገር ቤት እነ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም፣ በውጭ ሀገር ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ደርጅቶች እንደሚሉት፣ ከምርጫው ደግሞ እራሳችን ብናገል ምን ጥቅም እናገኛለን? ወደ ምርጫው አለመግባታችን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሊያስፈታ ይችላልን?

 

ቁም ነገሩ ምርጫ መግባቱና አለመግባቱ ላይ አይደለም። እኛ አንድነትና ጥንካሬ ከሌለን ምርጫ ገባን አልገባን ምንም ለውጥ አናመጣም። በመሆኑም ምርጫው እንደ ትልቅ ነገር ተደርጉ መታየት የለበትም ባይ ነኝ።

 

ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ከተቆናጠጠ አሥራ ስምንት ዓመት አልፎታል። (ደርግ በሥልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ የበለጠ) አንዳንዶቻችን ይህ የሆነበት ምክንያት ጠመንጃ ስላለው ነው እንላለን። አይደለም! ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ ያለው በተለያዩ መንገዶች ህዝቡንና ጠንካራ ተቃዋሚዎችን መከፋፈል በመቻሉ ነው።

 

አሁንም ከአሥር ወራት በኋላ ይደረጋል የሚባለው ምርጫ እየከፋፈለን እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። “ብርቱካን ሚደቅሳ ካልተፈታች ምርጫ አንገባም፣ ወይም እንገባለን” እያለን የምንጨቃጨቅና የምንከፋፈል ከሆነ፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር እስከ አሁን እንደነበረው የአንድነታችን ምክንያት መሆኑ ይቀርና የመለያየታችን ምክንያት እየሆነ በመምጣት ላይ እንዳለ እናያለን። እኔ እንደማምነው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችው ለዚህ አልነበረም።

 

ገዥው ፓርቲም እርሷን በግፍ አስሮ እርሷ ካልተፈታች “ምርጫ እንግባ? አንግባ?” የሚል ግጭት በተቃዋሚዎች ውስጥ በቀላሉ መዝራት ከቻለ፣ ገዢው ፓርቲ እርሷን የሚፈታበት ምንም ምክንያት አይኖረውም። የርሷ መታሰር አሁን እንዳለው ተቃዋሚዎችን የሚሰነጣጥቅ ከሆነ፣ እርስ በርስ እያጋጨ ሥልጣኑን ያራዝማል እንጂ፣ ምን ቸገረውና ብርቱካን ሚደቅሳን ይፈታታል። ደግሜ እጠይቃለሁ - በዚህ ሁኔታ ወያኔ/ኢህአዲግ ለምንድን ነው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የሚፈታት?

 

ስለዚህ ከአሥር ወራት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ዙሪያ አሁን እየተደረገ ያለው ክርክር ትግሉን የሚጠቅም ክርክር ሳይሆን ትግሉን የሚጎዳ፣ የምንወዳትና የምናከበራት የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የቃሊቲ አሰቃቂ ኑሮን የሚያራዝም፣ እንደ አይጋ ፎረም ያሉ አፍቃሪ አምባገነኖችን ጮቤ የሚያስረግጥና ያለ ምንም ጥርጥር ገዢውን ፓርቲ የሚጠቅም ወቅታዊ ያልሆነ ክርክር ነው።

 

ስለሆነም ሁላችንም ቆም ብለን እንድናስብና መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለራሳችን እንድንጠይቅ ያስፈልጋል።

 

ይህን ብዬ ወደፊት እንድንራመድ ይረዳን ዘንድ፣ ይጠቅማሉ የምላቸውን የሚከተሉት ስምንት ሃሳቦች በአክብሮት አቀርባለሁ።

 

1. ምርጫው አሥር ወራት ይቀሩታል። በመድረክ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች እንዲሁም መኢአድ በምርጫ እንሳተፋለን ወይም አንሳተፍም የሚሉ አስተያየቶችን ከመስጠት ተቆጥበው፣ ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጋራ እንዲሠሩ ያስፈልጋል። በምርጫው ወቅት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔት መሆኑ ግንዛቤ ላይ ከተደረሰ፣ ባለፈው የወረዳና የማሟያ ምርጫ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ያኔ በጋራ እራሳቸውን ከምርጫው ያገላሉ። በምርጫው መሳተፍ ጥቅም ካለው ደግሞ በጋራ ወደ ምርጫው ይገባሉ። ይህንን ውሳኔ በጊዜው እንዲወስኑ ለነርሱ እንተውላቸው።

 

2. በሀገር ቤት የሚኖሩ ተቃዋሚዎች ለምርጫው ከአሁን ጀምሮ፣ ምርጫ እንደሚሳተፉ በመገመት መዘጋጀት፣ የምርጫ ስትራቴጂ ማውጣት፣ ተወዳዳሪዎችን መመደብ፣ ህዝብን ማስተባበር ይኖርባቸዋል።

 

3. ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚደረገው ድርድር መቋረጥ የለበትም። ምርጫውን በተመለከተ እስከሆነ ድረስ ድርድሮችን መካፈሉ ችግሩ አይታየኝም። አላወቅንበትም እንጂ ገዢው ፓርቲ ድርድሩን በመኢአድና በመድረክ መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር እየተጠቀመበት ነው። ስለዚህ በሚቀርቡ አጀንዳዎች ሁሉ ላይ መወያየት እስከተቻለ ድረስ፣ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔት መድረኩ ወደ ድርድሩ ገብቶ ከመኢአድ ጋር አብሮ መሥራት ይኖርበታል ባይ ነኝ።

 

4. በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመሩት መኢአድ የመድረኩ አባል ድርጅት ሆኖ የሚሠራበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል። ይህም ካልተቻለ ደግሞ መድረኩና መኢአድ ከገዥው ፓርቲ ጋርም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በሚያደርጉት ውይይት በጋር በመሰለፍ የጋራ አቋም ማሳየት ይኖርባቸዋል። በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በዚህ ረገድ ፓርቲዎቹን ትልቅ ግፊት ማድረግ ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ።

 

5. የአንድነት ፓርቲ፣ ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያምን ጨምሮ በርካታ የድርጅቱ የምክር ቤት አባላትን ከፓርቲው አግዷል። ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያምና አብረዋቸው ያሉ በአንድነት የሥራ አስፈጻሚው ኮሜቴ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ወገኖች፣ አልተሳሳቱም ባልልም፣ ከደርጅቱ መታገዳቸው ግን የአንድነት ፓርቲን ያዳከመና ጠቃሚ ያልሆነ ውሳኔ ነው ባይ ነኝ። የተወሰደውም ውሳኔ ምን ያህል የድርጅቱን ሕግና ደንብ እንደጠበቀ በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም።

 

እነ ፕሮፌሠር መስፍን፣ ያለውን ችግር በውይይት ለመፍታት ፍቃደኝነታቸውን እንደገለጹ አውራምባ ታይምስ ዘግቧል። በመሆኑም አሁን ያሉት የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት በሌሎች የድርጅቱ አመራር አባላት ላይ የወሰዱትን እርምጃ ቀልብሰው፣ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ችግር በውይይትና በንግግር መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።

 

የአንድነት ፓርቲ የሠለጠነ ፖለቲካን የሚያራምድ ፓርቲ ነው። ችግሮችን በንግግር መፍታት ሊያቅተው አይገባም። የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት አብረዋቸው ፓርቲውን ከመሰረቱና አብረዋቸው ብዙ መስዋዕትነትን ከከፈሉ የአንድነት መሥራች ወገኖች ጋር አብረው መሥራትና ችግሮቻቸውን በንግግር መፍታት ካልቻሉ፣ በመድረኩ ውስጥ ካሉ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በዘላቂነት አብረው ይሠራሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በጥቂቱ ያልታመነ በብዙ እንዴት ሊሾም ይችላል? (በዚህ አጋጣሚ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የአንድነት ደጋፊዎች ጭፍን ድጋፍ ለፓርቲው ከመስጠት ተቆጥበን ፓርቲው ለድርጅቱ የሚጠቅመውን መንገድ እንዲከተል ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ይኖርብናል። ፓርቲው የድርጅቱ የአመራር አባላቱ ብቻ አይደለም።)

 

6. አቶ አሥራት ጣሴ እንዳሉት ምርጫ በማሸነፍ ወ/ት ብርቱካንን እናስፈታለን የሚለው አባባል ተቀባይነት የሌለው አባባል ነው። ምርጫ ተደረገም፣ አልተደረገም ይችን ታላቅና ጀግና ሴት ለማስፈታት፣ ከምርጫው ጋር ያልተገናኘ፣ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ማጧጧፍ ያስፈልጋል። የውጭ ዲፕሎማቶችን ከማነጋገር፣ አንድ በአባላት ብቻ የተደረገ ሰልፍ ከማድረግና በጽ/ቤት ውስጥ በየወሩ ከሚደረግ የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ውጭ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለማስፈታት ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሲደረግ አላየሁም። እውነቱን እንነጋገር ህዝቡን እንደሚገባ አላንቀሳቀስነውም።

 

በዚህ ረገድ የአንድነት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የመድረክ አባል ደርጅቶች ሁሉ እንዲሁም በኢ/ር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ ትልቅ ትኩረት ሰጥተውበት የተቀናጀ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች መጀመር ይጠበቅባቸዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርና መሪ ብቻ አይደለችም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የመኢአድ፣ የአንድነት፣ የዓረና፣ የኦብኮ፣ … መሪም ናት። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዳግማዊት ጣያቱ ብጡል፣ የሁላችንም መሪ ናት።

 

7. በውጭ ሀገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የፖለቲካ መድረኮች ምርጫውን በተመለከተ በየጊዜው ከሚያወጡት መግለጫ እራሳቸውን እንዲቆጥቡ ያስፈልጋል። በሀገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን ናቸው አፈና፣ ችግር፣ እስር እየገጠማቸው፣ እየታገሉ ያሉት። “ወደ ምርጫው መግባት ያስፈልጋል፣ አያስፈልግም” ለሚሉት ጥያቄዎች፣ በጊዜውና በሰዓቱ እነርሱ እራሳቸው የሚወስኑት ይሆናል። አሁን ማንሳት የማያስፈልገንን ነጥብ እያነሳን አላስፈላጊ ጭቅጭቅና ትርምስ ከመፍጠርና፣ ለገዢው ፓርቲ መጠቀሚያ ከመሆን መቆጠብ ይኖርብናል። አንርሳው - ገዢው ፓርቲ ጥንካሬ የኛ መከፋፈል ነው።

 

8. በኢትዮጵያ ያሉ ወገኖቻችን፣ አገዛዙ ፍፁም አምባገነንና ግትር ከመሆኑ የተነሳ የህዝቡ ሰቆቃና ስቃይ እየጨመረ ከመጣ፣ የፊታችን ምርጫም እንኳን በ97 ወደ ነበረው አይነት ሊቃረብ ቀርቶ ፍፁም አፈና የበዛበት ከሆነ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም እራሳቸውን ከምርጫው ያገላሉ የሚል ግምት አለኝ።

 

ተቃዋሚዎቹ እራሳቸውን ከምርጫው ካገለሉ ደግሞ ገዢው ፓርቲ በፎርፌ ብቻውን፣ ወይንም ከነአየለ ጫሚሶ ጋር ተወዳደሮ አሸነፍኩ ማለቱ አይቀርም። የውጭ ኃይላትም አገዛዙ ጥቅማቸውን እስከጠበቀ ድረስ ይቃወሙታል ብዬ እራሴን አላሞኝም። በኢራን እንደታየው ከተቃወሙም ተቃውሟቸው ለትንሽ ጊዜ ብቻ ነው የሚሆነው። ጥቂት ሣምንታት እንዳለፉም ዝም ማለታቸውና ገዥውን ፓርቲ በእርዳታ ማንበሽበሻቸው አይቀርም። የማታ ማታ ባዷችንን ልንቀር ነው ማለት ነው።

 

ስለዚህ በውጭ ሀገር ያለን ኢትዮጵያውያን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን ትግል ሙሉ ለሙሉ እየደገፍን፣ የሚደረገው ጥረት ተገቢውን ውጤት ካላመጣ አማራጭ መንገዶችን (PLAN B) ከአሁኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል።

 

ለዚህም እንዲረዳ በአስቸኳይ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለድርድር ያላቀረበ ትብብር መፈጠር ይኖርበታል ባይ ነኝ። ይህ ትብብር “ምርጫው ከተጭበረበረና አገዛዙ የዘረጋውን አፈና ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምንም ማድረግ ካልቻሉ፣ እነ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ካልተፈቱ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?” ለሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥና ትግሉን ወደ ምዕራፍ ሁለት የሚወስድ ይሆናል።

 

እዚህ ላይ ትብብር እንፍጠር ስል “ትብብር እንፍጠር” እያልን ለዓመታት እናውራ ማለቴ አይደለም። ውጭ ሀገር ባሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ስንሰማ የከረምነው የእንተባበርን ጥሪ መስማት ያልሰለቸው ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። የምንፈልገው ሁላችንንም ያደከመን የ“ትብብር እናድርግ” ወሬ ሳይሆን በተግባርና በሥራ ላይ የዋለ ትብብርን ነው።

 

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

አገዛዙ ተከፋፈሉ ሲለን አሜን ብለን መከፋፈል ማቆም አለብን። በዘር መከፋፈል መቆም አለበት። ምርጫ እንግባ አንግባ የሚል መከፋፈል መቆም አለበት። ሠላምዊ ትግል ይጠቅማል አይጠቅም የሚል መከፋፈል መቆም አለበት። በግለሰቦች ተክለ ሰውነት ምክንያት የተፈጠሩ መከፋፈሎች መቆም አለባቸው።

 

ሁላችንም የድርሻችንን እንሥራ። ሁላችንም በሌላው ሥራ ጣልቃ አንግባ። ሁላችንም ልዩነቶቻችንን እንደያዝን መስማማት በምንችለበት ጉዳዮች ላይ አብረን እንሰለፍ። ሌላውን ከማጥቃትና ከመቃወም እኛ የሠራነውን ሥራ በተግባርና በተጨባጭ እናሳይ። እኛ የድርሻችንን ሳንወጣ የሚሠሩ ሌሎችን አናጣጥል። ትላንት ያጠፋን ካለንም ዛሬ አስተዋጽዖ ማድረግ ስንችል፣ በትላንት ጥፋታችን እየተደጋገመ አንኮነን። በትንሹም በትልቁም ልዩነት ሲፈጠር ለክስና “ወያኔ ነው!” ለማለት አንቸኩል። እርስ በርስ በቅንነት እንቀባበል። የበሰልንና የነገውን የምናይ እንጂ ወደ ኋላ የምናስብ፣ ትላንት የሠራናቸውን ስህተቶች እየደጋገምን የምንሠራ፣ የማንማር ሰዎች አንሁን!

እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን!


ግርማ ካሣ

ጥቅምት 3 ቀን 2002 ዓ.ም.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ