የምርጫ ውጤቱን ወደ አዲስ አበባ ለማስመጣት ምርጫ ቦርድ ትብብር ጠየቀ
የምርጫ ሳጥኖች
ለጸጥታ ኃይሎችና ለሹፌሮች ቦርዱ አበል ይከፍላል
ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 22, 2021)፦ ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ትናንት በሰላም መጠናቀቁ ከተገለጸ ወዲህ፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤቶችን ከክልል ወደ አዲስ አበባ በልዩ ጥበቃ እንዲገቡ የክልል መንግሥታትን ጠየቀ።
ቦርዱ ከደቂቃዎች በፊት ለየክልሎቹ በጻፈው ደብዳቤ የጥበቃና የእጀባን ሥራ ለሚያከናውኑ የጸጥታ ኃይሎች እና ሹፌሮች ቦርዱ አበል የሚከፍል ስለመኾኑም ገልጿል።
በትናንትናው ዕለት (ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) በተደረገው ምርጫ 2013 መሠረት የተደመረው የየምርጫ ጣቢያው ውጤቶች ወደ ክልሎች እየተላኩ ሲሆን፤ ከክልሎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንዲጓጓዙ የሚደረግ በመኾኑ፤ በዚሁ መሠረት ምርጫ ቦርድ ይህንን የማጓጓዣ ሥራ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ጠይቋል።
ዛሬ ምርጫ በተካሔደባቸው አካባቢዎች ጊዜያዊ ውጤቶች የተለጠፉ ሲሆን፣ አጠቃላይ የጊዜያዊ ውጤቱን ደግሞ ምርጫ ቦርድ በሕግ በተሰጠው በአሥር ቀናት ውስጥ የሚያሳውቅ እንደኾነ ይታወቃል።
ኾኖም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሶሻያ ሚዲያዎች የሚለቀቁ አንዳንድ መረጃዎች ተገቢ ያለመኾናቸውንና በወንጀል የሚያስጠይቁ በመኾኑ፤ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን በይፋ እስኪያስታውቅ ድረስ ከዚህ አድራጐት እንዲቆጠቡ ቦርዱ አሳስቧል። (ኢዛ)



