ኢትዮጵያ ባለድርሻ የኾነችበት የበርበራ ወደብ ተርሚናል ሥራ ጀመረ
ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ አቶ አሕመድ ሸዴ፣ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ፣ የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን እና አቶ ሙስጠፌ መሐመድ (ከግራ ወደቀኝ)
ኢትዮጵያ 19%፣ ሶማሌላንድ 30% እና ዲፒ ወርልድ 51% ድርሻ አላቸው
ኢዛ (ሐሙስ ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 24, 2021)፦ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ በኢትዮጵያ አሥራ ዘጠኝ በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የተያዘው የበርበራ ተርሚናል ኮሪደርና የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት ጀመረ። ቀሪው ድርሻ 30 በመቶ የሶማሌላንድ ሲሆን፣ 51 በመቶ ደግሞ የዲፒ ወርልድ እንደኾነ ታውቋል።
በዛሬው ዕለት (ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም.) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ በተገኙበት በይፋ የተመረቀው ይህ ኮሪደር፤ በዓመት አንድ ሚሊዮን ኮንቴነሮችን ማስተናገድ የሚችል መኾኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያን ታሳቢ በማድረግ ጭምር የታሰበውና ባለቤት የኾነችበት ይህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ዘመናዊ የሚባሉ መሣሪያዎች የተገጠመላት ሲሆን፤ አማራጭ የኢትዮጵያ ወደብ ይኾናል። በተለይ ለምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የዚህ ወደብ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ያለውም ነው።
ወደቡ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ከሚያስገኘው ገቢም ኢትዮጵያን የጥቅም ተጋሪ የሚያደርጋት ይኾናል።
ዛሬ በይፋ በተመረቀው ኮሪደር ላይ ከኢትዮጵያ ወገን የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የሶማሌ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሸዴ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ኾነው ኮሪደሩን በይፋ ሥራ አስጀምረዋል። (ኢዛ)



