Teddy Afroዳኛ መሐመድ ዑመር ተነስተው የቀድሞው ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ተተኩ

  ቴዲ አፍሮ የፊታችን ሰኞ ውሳኔ ላያገኝ ይችላል

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም. October 30, 2008)፦ የዝነኛውን የአርቲስት ቴድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) ችሎት ሲያዩ የነበሩት የቀድሞው ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ከዚህ በኋላ የሚኖሩትን የቴዲን ችሎቶች በዳኝነት እንደሚመሩ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ። ያለፉትን ሁለት ችሎቶች ብቻ ሲያስችሉ የነበሩት ዳኛ መሐመድ ዑመር ከትናንት ጥቅምት 19 ጀምሮ የቴዲ አፍሮ ጉዳይ ከሚታይበት ችሎት ተነስተዋል።

 

ዳኛ መሐመድ ዑመር ”... ከመስከረም 22 ጀምሮ ሌላ ተለዋጭ ቦታ እስኪሰጥዎ ድረስ በጊዜያዊነት በ8ኛ ችሎት ተመድበዋል” የሚል ደብዳቤ ደርሷቸው ስለነበር፤ በቀድሞው ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ምትክ መስከረም 29 ቀን እና ጥቅምት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. የዋለውን የቴዲ አፍሮን ችሎት በዳኝነት መርተዋል። በሁለቱ ችሎቶች የቴዲ ጠበቃ ያቀረባቸውን የመከላከያ ማስረጃዎችና ተከሳሹን ቴዲ አፍሮን ጨምሮ የስምንት የምስክሮች ቃል ተደምጧል። ዳኛ መሐመድም ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ቀጥረው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።

 

ጥቅምት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. በተፃፈ ደብዳቤ ደግሞ ከጥቅምት 19 ቀን (ትናንት) 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ዳኛ መሐመድ ዑመር ወደ ፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት በጊዜያዊነት መመደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።

 

ከሁለቱ ችሎቶች በፊት ቴዲ አፍሮ ፍርድ ቤት ከቀረበበትና ከታሰረበት ከሚያዝያ 8 ቀን ጀምሮ ችሎቱን በዳኝነት ይመሩ የነበሩት ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ለሕክምና ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጉዘው የነበረ ሲሆን፣ ሕክምናቸውን ጨርሰው በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ታውቋል። በዚህም ምክንያት ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ወደ ሥራቸው የተመለሱና የፊታችን ሰኞ የቴዲ አፍሮን ችሎት እንደሚያዩ ለማወቅ ችለናል።

 

እንደ የኢትዮጵያ ዛሬ ታማኝ ምንጮች ገለጻ ከሆነ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም የውሳኔ መዝገቡን ተረክበዋል። ምንም እንኳን የፊታችን ሰኞ የቴዲ አፍሮ ክስ ውሳኔ ሊሰጥበት የተቀጠረ ቢሆንም፤ በዚህ በተፈጠረው ምክንያት በዕለቱ ውሳኔ ላያገኝ እንደሚችልና፣ ዳኛ ልዑል ”መዝገቡን አላየሁትም፤ አልመረመርኩትም” ሊሉ እንደሚችሉ ተገምቷል።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ያነጋገራቸው ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ፤ ዳኛ መሐመድ ዑመር ረጋ ያሉ፣ ሰው የሚያዳምጡ፣ ለሁሉም የመደመጥ ዕድል የሚሰጡ፣ ሁሉንም በእኩል የሚያዩ፣ ... በመሆናቸው ችሎቱን የሚከታተሉም ሆኑ የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎች በዳኝነት ችሎቱን በማስቻላቸው ተደስተው ነበር። ይህንን የዳኛውን ከችሎቱ መነሳት ዜና ሲሰሙ ብዙዎች እንደማይደሰቱ ተገምቷል። በተለይም የቴዲ አፍሮ ቤተሰቦችና ወዳጆች ጉዳዩ የበለጠ ሊያሳስባቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።

 

በድጋሚ የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚይዙትና ውሳኔ የሚሰጡት ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ የቅንጅት መሪዎችን፣ የጋዜጠኞችን፣ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎችን ክስ ካዩት ዳኞች መካከል የቀኝ ዳኛ ሆነው ተሰይመው የነበሩ ናቸው። ዳኛው በብዙዎች ዘንድ በአስቸጋሪነታቸው ይታወቃሉ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ