የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ነገ ይመክራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ
የዐረብ ሊግ አገራት ጣልቃ ገብነትን ኢትዮጵያ አውግዛለች
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 7, 2021)፦ ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ የውኃ ሙሌት መጀመሯ በተሰማ ማግሥት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ነገ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ለመወያየት ውሳኔ ላይ የደረሰው በግብጽና በሱዳን ጥያቄ መሠረት እንደኾነም ተገልጿል።
የጸጥታው ምክር ቤት የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በአጀንዳነት ይዞ ይወያያል መባሉ ከምክር ቤቱ ሥልጣን በላይ ስለመኾኑ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ይህንን ተቃውማለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የጸጥታው ምክር ቤትና የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ እንዲገቡ በዐረብ ሊግ አገራት መጠየቃቸውን በመቃወም የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በደብዳቤ አሳውቋል።
የዐረብ ሊግ አገራት በደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤትና ለተመድ የጠየቁት ጥያቄን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት እንዳስታወቀው፤ የዐረብ ሊግ አገራት በተመድ ሊታይ የማይገባውን ጉዳይ ማንሳታቸውም ተገቢ እንዳልኾነ ገልጿል። የዐረብ ሊግ አገራት በግድቡ ጉዳይ ከግብጽ ጋር መቆማቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ድርጊት ኢትዮጵያ በእጅጉ በማውገዝ ማስታወቅዋ አይዘነጋም። ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በተጀመረው መንገድ መቀጠል አለበት የሚለውን አቋሟንም ተመድ እንዲያውቅ አድርጋለች።
ትናንት ለተመድ ከኢትዮጵያ የተላከው ደብዳቤ ውስጥ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት በኩል ድርድሩ በሦስትዮሽ እየተከናወነ ስለኾነ የዓረብ ሊግ አገራት እየሔዱበት ያለው መንገድ የአፍሪካ ሕብረትንና የዐረብ ሊግ ግንኙነትን አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑን ነው። (ኢዛ)



