ቴዲ አፍሮ ለ28 ቀናት በእስር ይቆያል
"መዝገቡን መርምረን አልጨረስንም" ዳኛ ልዑል
ለኅዳር 22 ተቀጠረ
ነፃ የወጣበት የስዕል ክስ ተሸሮ ይከላከል ተባለ

Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. November 3, 2008)፦ ልደታ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቴዲ አፍሮ ችሎት በሚታይባቸው ቀናት የፍርድ ቤቱ ቅጽር ግቢም ሆነ ውጪው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግባቸዋል። በህዝብም ይጨናነቃሉ። ዛሬም አካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ይታይበት ነበር።
ችሎቱ የተቀጠረው ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር 7 ሰዓት ተኩል ላይ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ ቅጽር ቅቢ ከምሳ ሰዓት በፊት ጀምሮ ተጨናንቆ ነበር የዋለው። ከፍርድ ቤቱ ውጪ የፌደራል ፖሊሶች አካባቢውን ወረውታል። ስነሥርዓት ለማስከበርና አካባቢውን ለመጠበቅ በርካታ የትራፊክ ፖሊሶች፣ መደበኛ ፖሊሶችና የችሎት ፖሊሶች በሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
የችሎቱ መግቢያ ሰዓት 7፡30 ላይ በመሆኑ የችሎቱ በራፍ ሲከፈት አካባቢውን አጨናንቀውት ከነበሩት ውስጥ ጥቂቶች መግባት ቻልን። ችሎቱ በደቂቃ ውስጥ ግጥም ብሎ ሞላ። እጅግ በጣም ብዙ ሰው ችሎቱ በመሙላቱ ከበር ላይ ተመልሷል። የመግባት ዕድል ያልገጠማቸው የቴዲ አፍሮ አፍቃሪዎች፣ ደጋፊዎችና ችሎቱን ለመከታተል የመጡ በርካታ ሰዎች ግን የችሎቱን አካባቢም ሆነ የፍርድ ቤቱን ቅጽር ግቢ ለቅቀው አልወጡም።
7፡55 ሰዓት ላይ ታዋቂው አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) የማረሚያ ቤት ፖሊሶች በመኪና አጅበውት ፍርድ ቤቱ ደረሱ። ቴዲ አፍሮ ጥቁር የፀኃይ መነጽርና ጥቁር ሰማያዊ ኮትና ሱሪ ለብሶ በፖሊሶች እንደታጀበ ለህዝቡ ሠላምታ እየሰጠ ወደ ችሎቱ ገባ። ሁሉም የዛሬውን የመጨረሻ ውሳኔ በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቅ ስለነበር ህዝቡ ለቴዲ አፍሮ ሠላምታ ከወትሮው የተለየ ምንም አይነት ምላሽ ባይሰጠውም የችሎቱ ታዳሚዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው ተቀብለውታል።
ከዚህ ቀደም በዋሉት ችሎቶች ቴዲ አፍሮ ቀድሞ ከገባ በኋላ ታዳሚው እንዲገባ ይደረግ የነበረ ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን በመሆኑ ያልተጠበቀ ግርግርና ሁካታ እንዳይፈጠር በመስጋት የችሎቱ ተከታታይ ታዳሚዎች ቀድመው እንዲገቡ ተደርጓል።
8፡00 ሰዓት ችሎት ተሰየመ
ከቀኑ በ8 ሰዓት ላይ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም መቀመጫቸውን በመያዝ ችሎቱ ተሰየመ። ”ለዛሬ የተቀጠረው ችሎት ለውሳኔ ነው። ነገር ግን መዝገቡን መርምረን ስላልጨረስን የቀጠሮ ቀን እንወስናለን” በማለት ቀጠሮ የሚመዘግቡበትን አጀንዳ አንስተው ማገላበጥ ጀመሩ።
በመጨረሻም የሚፈልጉት ገጽ ላይ ሲደርሱ ቀና ብለው ”ለኅዳር 22 ቀጥረናል” በማለት ተናገሩና ወደ ከሳሽና ተከሳሾች ተመለከቱ።
በዚህን ጊዜ ለቴዲ አፍሮ በቅርቡ የተቀጠሩለት ሁለተኛው ጠበቃ አመሃ በድሉ ”የቀጠሮ ጊዜው ረዘመ፤ ለአጭር ጊዜ ይሁንልን” በማለት የቴዲ አፍሮ ጠበቃ ሆነው ችሎት መቅረብ ከጀመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተያየት ሰጡ።
ዳኛ ልዑልም ”ተደራራቢ ሥራ አለብን፤ ይሄንን ብቻ አንሠራም” በማለት ምላሽ ሰጥተውና የጊዜ ቀጠሮውን አጽንተው ችሎቱን 8 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በትነውታል።
የመጨረሻ ውሳኔ
የፊታችን ኅዳር 22 ቴዲ አፍሮ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ባቀረበው የመከላከያ ማስረጃ ክሱን አልተከላከለም ካለ “ጥፋተኛ ነህ” በማለት የሚወስንበት ሲሆን፤ የቀረበው የመከላከያ ማስረጃ ክሱን በሚገባ ተከላክሏል ካለ ግን በዕለቱ በነፃ ያሰናብተዋል።
ኅዳር 22 ቀን ዳኛው ካልታመሙ ወይንም እክል ገጥሟቸው በሥራ ገበታቸው ላይ ካልተገኙ ቴዲ አፍሮ የመጨረሻውን ውሳኔ ሊያገኝ እንደሚችል ይታመናል። እስከሚቀጥለው ቀጠሮ ድረስ ቴዲ አፍሮ ለሚቀጥሉት 28 ቀናት በቃሊቲ እስር ቤት ታስሮ ይቆያል።
የስዕል ክሱ
በተያያዘ ዜና አቶ አዲስ ገብሩ የተባሉ ሰዓሊ ስዕሌ ያለ ፍቃዴ ተሰርቆ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ”ሰለሜ” በሚለው ክሊፕ ውስጥ አካቶ ሰርቶብኛል ሲሉ ክስ መስርተው የነበረና፤ በክሱም ከስዕሉ ላገኘው የነበረው ጥቅም ቀርቶብኛል፤ ስዕሎቼም በአግባቡ ባለመቅረባቸው የሞራል ጉዳት ደርሶብኛል በማለት የ700 ሺህ ብር ካሣ ጠይቀው በመጠየቅ መከራከሪያ ሲያቀርቡ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በወቅቱ በሰጠው ብይን የተከሳሹ ክስና ክርክር ውድቅ አድርጎ ከክሱ በነፃ አሰናብቶት እንደነበር ሐምሌ 25 ቀን 2000 ዓ.ም. መዘገባችን አይዘነጋም።
ከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን በነፃ ሊሰናበት አይገባም በማለት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ያስቀርባል ሲል ከተመለከተ በኋላ፤ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከክሱ በነፃ ሊሰናበት እንደማይገባና መከላከያውን እንዲያቀርብ ተወስኖበታል።



