ከ11 ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባል

Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 5 ቀን 2001 ዓ.ም. November 14, 2008)፦ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ”ነፃ” በተባለበት ሁለተኛው ክስ እንዲከላከል በይግባኝ የተወሰነ በመሆኑ ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን የመከላከያ ማስረጃዎቹን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ። የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ተሾመ ፀጋዬም ይቅረቡ ተብሏል።

 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ብርሃነ መስቀል ወጋሪ ሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. በሰጡት ትዕዛዝ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንና አቶ ተሾመ ፀጋዬ በዓቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ፣ እንዲከላከሉ የወሰነ በመሆኑ የመከላከያ ማስረጃቸውን ይዘው ይቅረቡ ብሏል።

 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥቅምት 19 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፤ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ አቶ ሺበሺ ይግዛው ይዘው የቀረቡትን የይግባኝ ማመልከቻ ተመልክቶ ”እንዲከላከሉ” የሚል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ክርክሩን መቀጠል እንዲያስችለው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ አስከፍቷል።

 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቴዲ አፍሮ በነፃ የተሰናበተበትን ብይን ሽሮ እንዲከላከል የሰጠው ውሳኔ፤ አንደኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን እና ሁለተኛ ተከሳሽ የኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ተሾመ ፀጋዬ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 1998 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት በልደታ ክ/ከተማ ቀበሌ 01/18 ልዩ ቦታው ቢረም ሜዳ አካባቢ ከሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ፣ የግል ተበዳይ የአቶ አዲስ ገብሩ የአዕምሮ የፈጠራ ሥራዎች የሆኑ አምስት ሥዕሎችን በሕገወጥ መንገድ ወስደው ”ሰለሜ” በተሰኘ የዘፈን አልበም (ክሊፕ) ውስጥ፣ ሁለት ጊዜ በቪሲዲ ለሽያጭ በቀረበ ዕትማቸው፣ ለሙዚቃው ማስተባበሪያነት በመጠቀም ለገበያ በማዋላቸው፣ ሁለቱንም ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ መብቶችን ጥሰዋል በሚል መከሰሳቸውን አስታውሷል።

 

አርቲስት ቴዎድሮስም ሆነ አቶ ተሾመ ፍርድ ቤት ቀርበው ”ጥፋተኛ አይደለንም” በማለታቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ሁለት ምስክሮች አቅርቦ ካስመሰከረና በቪሲዲ የተቀረፀው ቀርቦ ከታየ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ መዝግቡን መርምሮ ተከሳሾቹ ምንም አይነት የኢኮኖሚና የሞራል መብት ጥሰት እንዳላደረጉ በመግለፅ ሁለቱንም በነፃ አሠናብቷል ሲል በከፍተኛ ፍርድ ቤት የነበረውን ክርክር ያስታውሳል።

 

በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰየመው ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ ሁለቱንም ወገን አቅርቦ ካከራከረ በኋላ፤ የከፍተኛው ፍርድ ቤት (የሥር ፍርድ ቤት) ”ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጥሰት አልተደረገም” በሚል የሰጠው ውሳኔ አግባብ እንዳልሆነና በኦዲዬ ቪዥዋል ሥራ ውስጥ የተካተቱ ነገሮች እንደ አስተዋይአቸው ሁኔታ እየታየ፣ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ድርሻ እንደሚሰጣቸው ሕጉ በግልፅ እየደነገገ ”ለአንድ የሥራ ውጤት መብት ከሌላ የሥራ ውጤት ጋር ሲቀላቀል ምን ትርጉም እንደሚሰጠው በግልፅ አልተደነገገም” ማለቱ ተገቢ ሆኖ ስላልተገኘ፤ እንዲከላከሉ ብሏል።

 

በተጨማሪም ”የሠዓሊው አቶ አዲስ ሥዕሎች በሙዚቃ ክሊፑ ውስጥ የተለያየ ቅርፅ እና የጥራት መጓደል ደርሶባቸውና የሥዕሎቹ የሥራ ውጤት የማን እንደሆኑ የሚገልፀው የግል ተበዳይ ስም ተቆርጦ ወጥቷል” ተብሎ በተመሠከረበት ሁኔታ፣ ፍርድ ቤቱ ”የሠዓሊውን ሞራል የሚነካ ድርጊት አልተፈፀመም” መባሉ ተገቢ አይደለም ሲል የጠቅላይ ፍርድ ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ መዝገቡ ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመልሶ ቀደም ሲል ክርክር ወዳልተደረገበት ሌላ ችሎት ተዛውሮ ጉዳዩ እንዲታይና ተከሳሾች እንዲከላከሉ ወስኗል።

 

ዓቃቤ ሕግ የውሳኔውን ግልባጭ በመያዝ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዲስ መዝገብ ያስከፈተ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ መዝገቡን ይዞ እንዲቀርብ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮና) አቶ ፀጋዬም የመከላከያ ማስረጃቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ታዟል።

 

ቴዲ አፍሮ በ8ኛ ወንጀል ችሎት ”በመኪና ሰው ገጭቶ ማምለጥ” በሚል ለቀረበበት ሌላኛው ክስ ለኅዳር 22 ቀን ለውሳኔ መቀጠሩ ይታወሳል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ