‘ባለሀብቶች ተሰብስበው ፌደሬሽን ነን በማለታቸው ውሳኔያችን አይቀየርም’ ፊፋ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2001 ዓ.ም. November 18, 2008)፦ ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት ሁለቱንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለማነጋገር በዙሪክ የተሰበሰበው ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ውሳኔው እንደማይቀየር አሳወቀ።

 

ውሳኔውን ለማስቀየር በእነሼህ አላሙዲንና በአቶ አብነት ከፍተኛ ድጋፍ ያለው አዲሱ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ያሲን እና አንድ ሌላ ባልደረባቸው በግል አውሮፕላን ዙሪክ በመገኘት ውሳኔውን ለማስቀየር ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ በፌደሬሽኑ እውቅና ያላቸው ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ መሆናቸውንና ጠቅላላ ስብሰባ በዶ/ር አሸብር ተጠርቶ ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ ምንም አይነት የውሳኔ ለውጥ እንደማያደርግ ፊፋ አስታውቋል።

 

በተጨማሪም ባለሀብቶች ተሰባስበው ፌደሬሽን ነን ብለው በቀረቡ ቁጥር እውቅና መስጠት ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን አሠራር አደጋ እንዳለው በአጽንዖት በማሳሰብ ያሰናበታቸው ሲሆን፣ ፊፋ እስካሁን የሚያውቀው በዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚመራውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እንጂ፤ አዲስ የተቋቋመውንና በባለሀብቶች የሚደገፈውንና አዲሱን አመራር እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል።

 

አቶ አህመድ ያሲን ከሌላ አንድ ግለሰብ ጋር ዙሪክ የተገኙ ሲሆን፣ "አዲስ አበባ ካሉ ባልደረቦቻችን ጋር ተመካክረን ውሳኔውን እናሳውቃለን" ማለታቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

ስብሰባው ለ30 ደቂቃ የቆየ ሲሆን፣ አዲሱ ፌደሬሽን በጠበቃቸው በኩል የፊፋን ውሳኔ አስቀይሬአለሁ ሲል ይደመጥ እንደነበር ይታወሳል።

 

ፊፋ ኢትዮጵያን የ2010 ዓለም አቀፍ ዋንጫ ማጣሪያን ጨምሮ የተለያዩ ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ ጥሎባት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ