ፊፋ ኢትዮጵያን ለስድስት ዓመታት ከማናቸውም ውድድሮች ያግዳታል
ኢትዮጵያ ለ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር የምታደርገውን የማጣሪያ ውድድር እንዳትካፈል ታገደች
Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. August 29, 2008)፦ አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር በተደጋጋሚ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡትም፣ የፊፋን ውሳኔ ሳያሟላና ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ለ2010 እ.ኤ.አ. የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ የታገደች ሲሆን፣ ምናልባትም ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ከማናቸውም ውድድሮች ልትታገድ እንደምትችል ፊፋ አስጠንቅቋል።
ፊፋ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ነኀሴ 21 ቀን 2000 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ለሚመለከታቸው ወገኖች በላከው ደብዳቤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በዛሬው ዕለት የፊፋን ውሳኔ መቀበሉን የማያሳውቀው ከሆነ ከዚህ ቀደም ላልተወሰነ ጊዜ ተብሎ የተጣለውን ገደብ ወደ ስድስት ዓመት ቅጣት ሊወስንበት እንደሚችል ገልጿል።
በዚሁ ደብዳቤ ላይ ፊፋም ሆነ ካፍ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተላከውን ፍኖተ ካርታ (ሮድ-ማፕ) ተግባራዊ ያደርጋል በሚል ሲጠባበቁ እንደነበር ጠቁሞ፤ ነገር ግን ይህን ተግባራዊ እንዳላደረጉ ገልጿል።
ለ2010 (እ.ኤ.አ) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከሞሮኮ ጋር ጳጉሜን 2 ቀን 2000 ዓ.ም. (September 7, 2008) አዲስ አበባ ላይ ልታደርገው ለነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ለመካፈል ከ10 ቀናት በፊት ማሳወቅ ሲገባት ባለማሳወቋና ውሳኔውንም አላከበረችም ሲል ፊፋ በዚሁ ደብዳቤ ገልጿል።
አክሎም ፊፋ በጉዳዩ ላይ የወሰነውን ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስከዛሬ ነኀሴ 23 ቀን ድረስ ማክበር አለማክበሩን የማያሳውቅ ከሆነ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ከማናቸውም የእግር ኳስ ውድድሮች ታግዳ እንደምትቆይ አስታውቋል።
በተጨማሪም በ2010ሩ የዓለም ዋንጫ ብቻ ሳይሆን በ2014 እ.ኤ.አ. የሚደረገውን የዓለም ዋንጫ እንዳትሳተፍ ታግዳ ትቆያለች ሲል ፊፋ ውሳኔውን አስታውቋል።ኢትዮጵያ በዚህ ቅጣት ከውድድሮች ብቻ ሳይሆን፤ ከፊፋ የሚገኝ ማንኛውንም ጥቅማ ጥቅሞች እንዳታገኝ ይደረጋል እንዲሁም ከማንኛውም ሀገር የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ግንኙነት እንዳታደርግም ትታገዳለች።
አዲሱ የፌዴሬሽን አመራር በጉዳዩ ላይ የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ እንደሚሰጥ ሲገልጽ፤ ዶ/ር አሸብር በበኩላቸው “ጠቅላላ ጉባዔ የተጠራው ውሣኔው ከተወሰነ በኋላ ለይስሙላ ነው።” ብለዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተፈጠረውን አለመግባባት ለማብረድ በርካታ ጥረቶችን ማድረጉን የሚገልፀው ፊፋ፤ ውዝግቡን ለመፍታት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) በማዘጋጀት ተግባራዊ እንዲደረግ ልኮ የነበረ ቢሆንም አዲሱ አመራር ይህን እንደማይቀበል ሲገልጽ ቆይቷል።
የፊፋ ፍኖተ ካርታ የሚለው፣ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር አሽብር ወ/ጊዮርጊስን አስወጥቶ ቢሮውን የተቆጣጠረውን ቡድን እንደማያውቀው፤ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መቀየር ካስፈለገም ዶ/ር አሽብር ቦታውን ተረክበው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራና አዲስ ምርጫ እንዲደረግ የሚያዝ ነበር።
ፊፋ በዛሬው ዕለት በሰጠው ውሳኔ ኢትዮጵያ ለ2010 (እ.ኤ.አ.) የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሞሮኮ ጋር የፊታችን ጳጉሜን 2 ቀን 2000 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ የምታደርገውን የእግር ኳስ ግጥሚያ መሰረዙን አስታውቋል።